አርዕስተ ዜና

ተሃድሶው የህዝቡን የስልጣን ባለቤትነት ያረጋገጠ መሆኑን የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ Featured

11 Jan 2017
536 times

ሶዶ ጥር 3/2009 በአካባቢያቸው የተካሄዱት የተሃድሶ ንቅናቄ መድረኮች በመንግስት ላይ ያላቸውን እምነት በማጠናከር የህዝቡን የስልጣን ባለቤትነት ያረጋገጡ መሆናቸውን  የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎች የተሳተፉበት የከተማ አቀፍ ተሃድሶ መድረክ ማጠቃለያ ውይይት ትናንት በሶዶ ተካሄዷል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የከተማው ጊዶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ኮርካ በሰጡት አስተያየት ሞጋች ህብረተሰብ መፈጠሩ የስርዓቱ ዉጤት መሆኑን ተናግረው የሰው መቀያየር ሳይሆን አስተሳሰቡ የተለወጠ  አመራር ለማምጣት  መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

" አመራሮቹ በህዝብ አስተያየት ተሰጥቶባቸው  ሃላፊነት እንዲወስዱ መደረጉ የመንግስትን ቁርጠኝነት ያመላከተና ህዝቡም ከመንግስት ጎን እንድቆም የሚያደርግ ነው" ብለዋል፡፡

ግልጽነት የሞላበት አሰራር በመዘርጋት የህዝብ ተሳትፎን ማሳደግና ዕድገት ማፋጠን እንደሚቻል ያመለከቱት አቶ ብርሃኑ የተሃድሶ መድረኩ  መንግስትና ህዝብ እንዲቀራረብ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

በሶዶ የአራዳ ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ሰርክአዲስ መለሰ በበኩሉ " የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ ላይ መሳተፌ የታሪክ ተጋሪ እንዲሆን አድርጎኛል" ብሏል፡፡

በተለይ መንግስትና ህዝብ አምኖ የሰጣቸዉን ስልጣን ለግል ጥቅማቸዉ ማስከበሪያ ያደረጉ ግለሰቦችን በግልጽ ህዝቡ አስተያየት እንዲሰጥባቸው መደረጉ ህዝባዊ መንግስት እንደሆነ እንደሚያመላክት ተናግሯል፡፡

"የተሀድሶ መድረኩ  አመራሩ ህዝብን እንዴት እየመራ እንደነበር ራሱን እንዲመለከት ያደረገ ፣ ከህዝብ  የሚያመልጥ እንደለለ ያሳየ ነዉ"  ያሉት ደግሞ  ወይዘሮ  አይናለም አሳሌ የተባሉት ነዋሪ ናቸው፡፡

የተሃድሶው ግምገማ ውጤት ለህዝብ መቅረቡ ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት እንዲጠናከርና ልማትን ለማፋጠን የሚረዳ መሆናንም ጠቅሰዋል፡፡

ሹመት ከመሰጠቱ አስቀድሞ ህዝቡ የሚመራው ማን እንደሆነ በማወቅ አስተያየት ሰጥቶበት እንዲወሰን መደረጉ የህዝቡን የስልጣን ባለቤትነት ያረጋገጠ መሆኑን ነዋሪዎቹ ጠቁመው ይሄው አካሄድ ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስራት ጤራ ህዝቡ የሚያነሳቸዉን ጥያቄዎች ተቀብሎ መንግስት ለማስተካከል የጀመረዉ እርምጃ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በተለይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መንግስት በሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ህዝብ በንቃት መሳተፍ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው  ጉድለቶችን ለማስተካከል ለተጀመው የተሀድሶ ንቅናቄ መሳካት የህዝቡ ተሳትፎ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ችግሮችን በማስተካካል የህዝብ አገልጋይነት ያለዉ አመራር ለማደራጀት በሚደረገው ጥረት ህዝቡ የሚመራውን እንዲያዉቅና አስተያየት እንዲሰጥ  ማድረጉ ግልጽነትን በመፍጠር  ህዝብና መንግስት የተሳሰሩ መሆናቸዉን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይም ለሹመት በቀረቡት  64 አመራሮች ላይ ነዋሪው ህዝብ አስተያየት ሰጥቶባቸዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር ምክር ቤት  ዛሬ በጠራው አስቸኳይ ጉባኤም አዲሶችን ጨምሮ በህዝቡ አስተያየት የተሰጠባቸው አመራሮችን ሹመት አጽድቋል፡፡

ተሿሚዎችም በምክር ቤቱ  ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ