የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የመሪነት ሚናችንን እንወጣለን - የደኢህዴን ሴቶች ሊግ አመራር አባላት

11 Jan 2017
564 times

አርባምንጭ ጥር 3/2009 የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚደረግ ጥረት የመሪነት ሚናቸውን እንደሚወጡ የጋሞ ጎፋ ዞን የደኢህዴን ሴቶች ሊግ አመራር አባላት ገለጹ፡፡

የሊጉ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአርባምንጭ ከተማ ውይይት አድርገዋል ፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ሴቶች ሊግ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዓለምነሽ ደመቀ እንደገለጹት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳታነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው ተግባር በበታችነትና በልዩነት መታየታቸው እየተቀረፈ መጥቷል፡፡

በቀጣይም ''ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ባስገኘው ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመን በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ዘርፎች ሴቶች አቅማቸውን በተግባር ማሳየት እንዲችሉ በትኩረት መስራት ይኖርብናል'' ብለዋል፡፡

ሴቶች ተደራጅተው በመንቀሳቀስ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኢኮኖሚ እየቀየሩ ቢሆንም ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ በትኩረት መስራት እንደሚጠይቅ የገለፁት ደግሞ የሊጉ አመራር ወይዘሮ ሳራ ኢዮብ ናቸው፡፡

በተለይ የድርብ ጋብቻ ችግር እናቶችን እየተፈታተነ በመሆኑ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል ፡፡

በማህበራዊ አገልግሎቱ በተለይ በወሊድ ምክንያት የአንድም እናት ህይወት እንዳያልፍ  በተከናወነው ተግባር ውጤት ቢመጣም አሁንም በዞኑ 16 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች የሚገላገሉት በቤት ውስጥ ነው፡፡

አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ በሚደረግ ጥረትም አደረጃጀቶችን በመጠቀም በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ አመራር ወይዘሮ እመቤት እሸቱ በበኩላቸው የምሁራን ሴቶች ቁጥር እያደገ በመምጣቱ የዞኑ ሴቶች በሙሳኔ ሰጪነት ያላቸው ድርሻ ከ30 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡

''ሥርዓቱ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ላይ የሴቶች ሚና የጎላ ነው'' ያሉት ኃላፊዋ የውሳኔ ሰጪነቱ ሚና ከዚህ በበለጠ ለማሳደግ በቀጣይ በሁሉም የልማት መስኮች ውጤት ማስመዝገብ እንዲቻል በተግባር የሚታይ ስራ መስራት እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡  

ተግዳሮቶችን በተደራጀ አኳኋን በመታገል በፀረ-ድህነት ትግሉ የሴቶች ሚና መጉላት እንደሚገባ የጠቆሙት ደግሞ ወይዘሮ የኔነሽ በላይ ናቸው፡፡

በፖለቲካና ኢኮኖሚ መስክ የሚታየውን የሴቶች ተሳትፎ ውስንነት ለመቅረፍ በተመደብንበት የሥራ መስክ ግንባር ቀደም መሆን ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ላለፉት ሁለት ቀናት የተካሄደውና ትናንት የተጠናቀቀው ውይይት ትኩረት ያደረገው ባለፉት 15 ዓመታት በተገኙ ድሎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም በቀጣይ ከሴቶች በሚጠበቁ ተግባራት ላይ ነው፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ