አርዕስተ ዜና

ባለስልጣኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ውይይት ማካሄድ ጀመረ

11 Jan 2017
518 times

አዲስ አበባ ጥር 3/2009 የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር፣ የውሃ መቆራረጥና ከአቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮች መፍታት የሚያስችል ውይይት ጀመረ።

ባለስልጣኑ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የሶስት ቀናት የጥልቅ ተሃድሶ ውይይት ትናንት ጀምሯል።

የባለስልጣኑ ሰራተኞች "ብቁና ውጤታማ ፐብሊክ ሰርቪስ ለሀገራዊ ህዳሴ" በሚል መሪ ቃል ነው ውይይቱን እያካሄዱ ያሉት።

ከዚህም ጠንካራ አፈፃጸም ያለው ፐብሊክ ሰርቪስ ለመገንባትና የአገሪቱን የለውጥ ጉዞ ማስቀጠል የሚያስችል አቅም እንደሚገኝበት ታምኗል።

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ሽመልስ መርጊያ በሰጡት አስተያየት ውይይቱ ከዚህ በፊት የውሃ ስርጭት ላይ ይስተዋል የነበረውን ችግር ለማቃለል የሚያስችል  ነው።

ባለስልጣኑ የማያቋርጥ የውሃ አቅርቦት ለከተማዋ ህብረተሰብ ለማድረስ እንዲችል ሁሉም ሰራተኛ የበኩሉን ለመወጣት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ወይዘሮ ፍጹም ሰይፉ በበኩላቸው አገሪቱ የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት በባለስልጣኑ ቀልጣፋና ጥራት ያለውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ከውሃ መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ከህብረተሰቡ የሚነሳውን ችግር ለመፍታት ጠንክረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም እንዲሁ።

በባለስልጣኑ የስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጸገነት ተስፋዬ እንዳሉት ህብረተሰቡን ሊያገለግል የሚችል ጠንካራ ሰራተኛ ለመፍጠር የአገልጋይነት መንፈስ የተላበስ ሰራተኛ እንዲሆን ለማድረግ የሚያግዝ ውይይት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ሰራተኛው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ችግርን ለማስወገድ ለአገሪቱ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ መወጣት አለበት ሲሉም ነው የተናገሩት።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ