አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ስልጠናው በመንግሥት ሰራተኞች ላይ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለማረም ያስችላል…ሚኒስትር ታገሰ ጫፎ Featured

11 Jan 2017
513 times

ጥር 3/2009 በሃገር ዓቀፍ ደረጃ ለሁሉም የመንግስት ሰራተኛ እየተሰጠ ያለው ስልጠና በሰራተኛው ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና የህዝብ አገልጋይነት ስሜትን የተላበሰ ሰራተኛ ለመፍጠር እንደሚያስችል የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ሚኒስትሩ አቶ ታገሰ ጫፎ አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት  የመንግሥት ሰራተኛው ሃገሪቱ በየዘርፉ ባስመዘገበችው እድገት ጉልህ ድርሻ አበርክቷል፡፡

ያም ሆኖ ግን ሰራተኛው የሚጠበቀውን ያህል የህዝብ አገልጋይነት መንፈስን ተላብሶ ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ባለመስጠቱ ህብረተሰቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል፡፡

ለህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ አለመስጠትና የህዝብ አገልጋይነት መንፈስን አለመላበስ እንዲሁም ኃላፊነትን ለግል ጥቅም  ማዋል በመንግሥት ሰራተኛው ላይ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ታገሰ፣ “በየክልሎቹና በየከተሞቹ ያለው የመንግሥት መዋቅር ተገልጋዩን የአገልጋይነት መንፈስ ተላብሶ ማገልገል ቢችል 70 ከመቶ የሚሆነው ችግር ይፈታል” ብለዋል፡፡

አሁን በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙ የመንግሥት ሰራተኞች እየተሰጠ ያለው ስልጠና የሰራተኛውን ጉድለቶች በማረምና የህዝብ አገልጋይነት አመለካከቱንም በማጎልበት ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

ስልጠናው የሃገሪቱ መንግሥት የሚከተለውን የልማትና የዲሞክራሲ አማራጮች ግልጽ ለማድረግና ፐብሊክ ሰርቪሱ አካባቢ የሚታዩ ብዥታዎችንም ለማጥራት የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት መንግሥት ሰራተኛው ላይ የተስተዋሉ ጉድለቶችን ነቅሶ በማውጣት ክፍተቶቹ የሚታረሙበትን የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥም ስልጠናው አስፈላጊ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ የሚመልስ፣ የለውጥ መሳሪያዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ አደራጅቶና አቀናጅቶ ጥቅም ላይ በማዋል ከሌሎች ሃገራት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል በአመለካከቱና በክህሎቱ በቁ የሆነ የመንግሥት ሰራተኛ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል አቶ ታገሰ፡፡

ባለፉት 25 ዓመታት “ሀገሪቱ በተጓዘችበት መንገድና ባሳካቻቸው ጉዳዮች ሁሉ የመንግሥት ሰራተኛው ትልቅ አስተዋጽኦ” ማበርከቱንም ሚኒስትሩ አውስተዋል፡፡

ለዚህም በመንግሥት መዋቅር  ውስጥ እቅድ ከማዘጋጀት ጀምሮ  እቅዱ ወደ ተግባር እስከሚመነዘር ያለውን ሂደት በመከታተልና አፈጻጸሙንም ገምግሞ ለቀጣይ የመንግሥት ውሳኔ  በሚያግዝ መልኩ የሚያደራጀው የመንግሥት ሰራተኛው  መሆኑን በአብነት አንስተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር አቶ ታገሰ ማብራሪያ የመንግሥት ሰራተኛውን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ባበረከተው አስተዋጽኦ ልክ ተጠቃሚ ለማድረግ በተለያየ ጊዜ  የሃገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም ያገናዘበ የማስተካከያ እርምጃ ተወስዷል፡፡

በቀጣይም የሀገሪቱን የኑሮ ሁኔታ በማጥናትና የመንግሥትንም የመክፈል አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት የመንግስት ሰራተኛውን ኑሮ ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትሩ ያረጋገጡት፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ