በሙስና ማስረጃ የቀረበበት የመንግሥት የሥራ ኃላፊ የሕግ ተጠያቂ ይሆናል---ጠቅላይ ሚኒስትሩ Featured

10 Jan 2017
567 times

አዲስ አበባ ጥር 1/2009(ኢዜአ) በሙስና ማስረጃ የቀረበበት በየትኛውም የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ የሚገኝ ግለሰብ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

የፀረ-ሙስና ትግሉን ለማገዝ አገራዊ የምርመራ ቢሮ ተቋቁሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ አገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ኢሕአዴግ እንደ ገዢ ፓርቲና እንደ መንግሥት ባደረገው ተሃድሶ ሙስና ፈጽመዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ በቂ እርምጃ አልወሰደም የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፤

መንግሥት ሙስና ፈጽሞ ማስረጃ በሚቀርብበት ማንኛውም ግለሰብ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አረጋግጠዋል።

ሙስና በባህርይው ውስብስብና ፊት ለፊት የሚደረግ ባለመሆኑ መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንዲያም ሆኖ መንግሥት በሚያገኘው መረጃና ማስረጃ መሰረት በየትኛውም የኃላፊነት እርከን ያለም ቢሆን ተጠያቂ እንዲሆን እያደረገ ነው ይላሉ።

"ማስረጃ ቀርቦበት በሕግ ተጠያቂ ከመሆን የሚቀር አንድም ሰው አይኖርም" ሲሉም ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ ከነበረበት ኃላፊነት ከማንሳት ጀምሮ በቂ መረጃ ሲቀርብ ሕግ ፊት ቀርቦ እንዲጠየቅ ይደረጋል ብለዋል።

"መንግሥት ባገኘው መረጃ ልክ ሙስና ፈፃሚዎችን ሕግ ፊት እያቀረበ ቢሆንም በቂ ነው ብሎ ግን አያምንም" ሲሉም ተደምጠዋል።

እናም መንግሥት የችግሩን ውስብስብነት ተገንዘቦ ሙስናና የሥነ-ምግባር ብልሹነትን ለመታገል በጥናት የተደገፈ ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሥርዓት መቀመጥ ያለበት ሌላው ጉዳይ ህዝቡ በፀረ-ሙስና ትግሉ በስፋትና በጥራት የሚሳተፍበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆኑን አስረድተዋል።

ይህን ማድረግ ከተቻለ በሙስና ዙሪያ ማስረጃዎችን ለማግኘት የሚያግዝ ይሆናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በዘርፉ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው የሙስናን ውስብስብነት ታሳቢ ያደረገና ህዝብ የሚጠቁምበትና መረጃ የሚሰጥበት መድረክ መፍጠር እንደሆነ በመጥቀስ።

ከዚህ አኳያ መንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ማዕከል በማቋቋም ህዝቡ በየጊዜው መረጃ የሚሰጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ወስኗል።

ከዚህ በተጓዳኝ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ኃብትና ንብረት ለህዝብ ይፋ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል።

ከተመዘገበው ውጭ በራሱ ይሁን በዘመድ አሊያም በተለያየ መንገድ የተያዘ ተጨማሪ ኃብት 'አለ' የሚል ሰው ካለ ይህን እንዲጠቁም የማመቻቸት ሥራ መንግሥት ይሰራል ነው ያሉት።

የፀረ-ሙስና ትግል አካል የሆኑ ተቋማት እንደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም የፖሊስ ኮሚሽንን ከማጠናከር ባለፈ እንደ አሜሪካ የፌዴራል ቢሮ ምርመራ አገራዊ የምርመራ ቢሮ እንዲቋቋም መደረጉንም ገልጸዋል።

እነዚህ ተቋማት በሰው ኃይልና በቁሳቁስ ተጠናክረው እንዲወጡና ጥቆማዎች ሲኖሩ በቂ ምርመራ እንዲያደርጉ ይደረጋል ብለዋል። 

በተጨማሪም ህዝቡ በኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥቆማ እንዲያደርግም ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቆሙት።

ትልቁ ጉዳይ በአሰራር ላይ ግልጽነት ማስፈን እንደመሆኑ ይህን ማድረግ የሚያስችል ተቋማዊ የግንባታ ሥራ መጀመሩንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የፀረ-ሙስና ትግሉን ውጤታማ ለማድረግ መንግሥት በዋናነት የሕዝብ አመለካካትና አስተሳሰብን መቀየር ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በኢሕአዴግ ተሃድሶ ላይ እንደ ድል የተወሰደው ምንም ድብቅ ነገር ሳይኖር ወደ መድረክ ቀርቦ ውይይት እንዲካሄድበት መደረጉ ነው ብለዋል።

"በመጀመሪያ ደረጃ ሙስና የአመለካከት መሸርሸር ውጤት እንደሆነ መረዳት ይገባል" ነው ያሉት። 

በቅርቡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 130 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ይታወቃል።

ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀሎችን መመርመር ከጀመረ በኋላ ከህዝብ፣ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት 260 የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች ደርሰውታል።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 125 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን መግለጹ የሚታወስ ነው።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል 22ቱ አመራሮች፣ 99ኞቹ ሠራተኞች ሲሆኑ አራቱ ደግሞ ተገልጋይ ግለሰቦች መሆናቸው በወቅቱ ተገልጿል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ