አርዕስተ ዜና

በሀገሪቱ ከአንድ ሚሊዮን 300ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት በደን መሸፈኑ ተገለጸ

467 times

ባህርዳር የካቲት 6/2010 በሀገሪቱ  ተራቁቶ የነበረ  ከአንድ ሚሊዮን 300ሺህ ሄክታር  በላይ  መሬት በደን መሸፈኑ የአካባቢ፣ የደን ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሩ ዶክተር ገመዶ ዳሌ አስታወቀ።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የክልሎች  የ2010 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሰድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም የሚገመግም መድረክ  በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

ሚኒስትሩ በዚህ ውቅት በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን  የተራቆተ መሬትን በደን የመሸፈን ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገው ጥረትም አካባቢያዊ ስነ ምህዳር መሰረት ያደረገ ችግኝ መተከሉን ጠቁመው በዚህም ከአንድ ሚሊዮን 300ሺህ ሄክታር  በላይ  ሄክታር በላይ መሬት በደን  መሸፈኑን ተናግረዋል።

የተራቆተ መሬት ለይቶ መልሶ በደን የማልበስ ስራ በሀገሪቱ በስፋት የሚከናወነው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል መሆኑን ጠቁመዋል።

የተፋሰስ ስራዎች ዘላቂነት ያለው ለውጥ ለማምጣት በሚያስችል መልኩ እንዲፈፀሙ በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንዳለባቸውም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

ባለፈው ክረምት በ664 ሺህ ሄክታር በተራቆተ መሬት ላይ የተተከለው  ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን  ችግኝ ውስጥ  70 በመቶ መጽደቁን የገለጹት ደግሞ በሚኒስቴሩ የደን ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ከበደ ይማም ናቸው።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጀመሪያ 15 ነጥብ አምስት በመቶ የነበረውን የሀገሪቱን የደን ሽፋን በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ 20 በመቶ ለማድረስ ግብ መያዙንም አስታውቀዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳላት የሚተከል ችግኝ  የመፅደቅ ምጣኔ እንዲጨምር  አርሶ አደሩ ተገቢ  ጥበቃና እንክብካቤ ማደረግ የሚያስችለው  ተከታታይ የግንዛቤ  ስራ እየተከናወነ ነው።

"በሀገሪቱ የደን ውድመትን ለመቀነስም በግማሽ ዓመቱ ከ535 ሺህ የሚበልጡ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ለተጠቃሚዎች እንዲሰራጭ ተደርጓል" ብለዋል።

በመጪው የክረምት ወቅትም ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት ላይ ለማልማት የችግኝ ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል።  

የአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና ዱር እንስሳት ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ በበኩላቸው ከአካባቢው ጋር ፈጥኖ የሚላመድ የደን ችግኝ  አርሶ አደሩ አልምቶ እንዲጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በተለይ፣ በአዊና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች የሚገኙ አርሶ አደሮች ደንን በስፋት በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩም ጠቅሰዋል፡፡

ለሶስት ቀናት በሚቆየው የገምገማው መድረክ የሚኒስቴሩና የሁሉም ክልሎች ያለፉት ስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚካሄድ ተመልክቷል።

 

 

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን