አርዕስተ ዜና

በሁለት ዞኖች ከ65ሺህ ሄክታር በላይ የተጎዳ መሬትን ለማልማት እየተሰራ ነው ተባለ

368 times

በሰሜን ወሎና ሰሜን ሸዋ ዞኖች በተያዘው የበጋ ወቅት አርሶ አደሩን በማሳተፍ ከ65ሺህ  ሄክታር በላይ  የተጎዳ መሬትን ለማልማት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ ነው፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን  የደን ልማት ባለሙያ አቶ መሀመድ አብደላ እንደገለጹት እስከ የካቲት 20/2010ዓ.ም በሚቆየው የልማት ስራ በጥናት በተለዩ 543 ተፋሰሶች ውስጥ ስራው የሚከናወን ሲሆን 388 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

እየተካሄዱ ካሉት ስራዎች መካከል የማሳና የጋራ ላይ እርከን ፣ የእርጥበት መቆያ ፣ ፣የክትር ስራ እና የውሃ ማሰባሰቢያ ኩሬ ቁፋሮ ይገኙበታል።

በዋድላ ወረዳ የቀበሌ ዜሮ ሁለት  አርሶ አደር ሰጠ በላይ በሰጡት አስተያየት የተከለሉ ቦታዎችን የአካባቢያዊ ህግ በማውጣት ከሌሎች ጋር በመሆን የመጠበቅና የመንከባከብ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት በተከናወኑ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች  የተጎዳው መሬት እያገገመ መሆኑን ጠቅሰው ልማቱ በተሰራባቸው የወል ይዞታዎችና የማሳ ዳር መሬት ለእንስሳት መኖ እየጠቀማቸው  መሆኑን ገልፀዋል።

ተፋሰስን መሰረት በማድረግ በተደጋጋሚ በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በላስታ ወረዳ የቀበሌ 23  ነዋሪና የተፋሰስ ኮሚቴ ጸሐፊ አርሶ አደር እንዳየነው ወርቀልኡል ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በሰሜን ሸዋ ዞን በ931 ተፋሰሶች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ በዞኑ ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም የስራ ሂደት መሪ አቶ ጌታነህ ሳህለ ማሪያም ናቸው።

በተፋሰሶች ውስጥም 35 ሺህ 100 ሄክታር መሬት ላይ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንና  ከ437 ሺህ በላይ ህዝብ እየተሳተፈበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል ፡፡

በሚለማው  መሬት ላይ በመጪው  የክረምት ወቅት የሚተከል  350 ሚሊዮን የእንስሳት መኖና  የደን ችግኝ እየተዘጋጀም መሆኑም ጨምረው አመልክተዋል፡፡

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን