አርዕስተ ዜና

በብዝኃ ሕይወት ላይ የተጋረጠውን ችግር ለመቋቋም የዘርፉ ምሁራን ማኅበር ሊመሰርቱ ነው

680 times

አዲስ አበባ የካቲት 6/2010 በኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ላይ ለተጋረጠው ዘርፈ ብዙ ችግር መፍትሄ ለማምጣት ተቀናጅቶ መስራት ያስፈልጋል ያሉ የዘርፉ ምሁራን፤ የብዝኃ ሕይወት ማኅበር ሊመሰርቱ መሆኑን ገለጹ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ መካነ አራዊት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አበበ ጌታሁን "በዱር እንስሳት ላይ የተጋረጠው አደጋ ውስብስብ ነው" ይላሉ።

የሰው ልጅ ኑሮውን ለመምራት በሚያደርገው ትግል ሁል ጊዜም ከዱር እንስሳት ጋር ግጭት መፍጠሩ አይቀሬ በመሆኑ እየጨመረ ያለው የሕዝብ ቁጥር ከብዝኃ ሕይወት ጋር የሚያደርገው ግጭት እየተባባሰ መምጣቱን ይገልጻሉ።

ሕዝብ መመገብና ብዝኀ ሕይወትን የመጠበቅ ስራ ተጣጥሞ እንዲሄድ የማስቻል ኃላፊነት የምሁራን የቤት ስራ መሆኑንም ያብራራሉ።

ብዝኃ ሕይወትን በመጠበቅ ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማምጣት አዳዲስ ሀሳቦችን ማመንጨት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ፕሮፌሰር አበበ መፍትሔ አመንጪ የሆነ የተመራማሪዎች ስብስብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የፕሮፌሰር አበበን ሃሳብ የሚጋሩት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ባልደረቦች ዶክተር ሽመልስ አይናለምና ዶክተር ደሳለኝ እጅጉ የዘርፉ ምሁራን ለዓመታት ያካሄዷቸውን ጥናትና ምርምሮች በማሰባሰብ ወደ ተግባር ለመተርጎም ማኅበር ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ።

የማኅበሩ መመስረት ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን በማፍለቅና በማማከር ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃው ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም አብራርተዋል።

ማኅበሩን ለመመስረት አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥናቶችን በመካሄድ ላይ ሲሆን ይኸው እንደተጠናቀቀ የዘርፉ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ምስረታው ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን