አርዕስተ ዜና

በጋምቤላ ክልል የመንግሰት ስራ ሰዓት ለውጥ ተደረገ

863 times

ጋምቤላ ጥር 30/5/2010 በጋምቤላ ክልል የሙቀት መጠን  እየጨመረ በመምጣቱ  የመንግሰት ስራ ሰዓት ለውጥ መደረጉን የክልል መስተዳድር ጽህፈት ቤት  አስታወቀ።

ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በክልሉ የሙቀት መጠኑ በመጨመሩና  የአየር ፀባዩ ለስራ አመቺ ባለመሆኑ ከነገ ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ የመንግሰት ስራ ሰዓት ለውጥ ተደርጓል።

በለወጡ መሰረትም የመንግሰት ስራ ሰዓት  መግቢያና መውጫ በመደበኛው ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እሰከ ስድስት ሰዓት ተኩል  የነበረው በለውጡ  ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እሰከ አምሰት ሰዓት ተኩል እንዲሆን የክልሉ መስተዳደር ወስኗል።

እንዲሁም ከሰዓት በኋላ በመደበኛው  ከዘጠኝ ሰዓት እሰከ 11 ሰዓት ተኩል የነበረው ከአስር ሰዓት እሰከ 12 ሰዓት ተኩል እንዲሆንም እንዲሁ።

የስራ ሰዓት ለውጡ ወይና አደጋ  የሆኑት የመጌሽና የጎደሬ ወረዳዎችን እንደማይጨምር መግለጫው ያመለክታል።

በብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ የጋምቤላ ክልል የሜትሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል እንደሚያመለክተው አሁን የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት 41 ዲግሪ ሴልሸስ ሲሆን የሌሊቱ ደግሞ 20  ዲግሪ ሴልሸስ ደርሷል።

ከዚህ በፊት  የቀኑ የሙቀት መጠን ከ35 እስከ 38 ሴልሸስ  የነበረ ሲሆን የሌሊቱ ግን ከአሁኑ እምብዛም ልዩነት እንደሌለው ነው የተጠቀሰው፡፡

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን