አርዕስተ ዜና

የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክን ከጥፋት ለመታደግ የአመራር ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

814 times

አርባ ምንጭ  ጥር 30/2010 የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ህልውናን ለመታደግ የአመራር ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ የጋሞ ጎፋ ዞን መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ ፓርኩ ለአደጋ የተጋለጠው በወሰን ማካለል ችግር በመሆኑ ዳግም የመከለል ሥራ እንደሚሰራ አመልክቷል፡፡

በጋሞ ጎፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የቱሪስት መስህብ ጥናትና ልማት ግብይት ዋና ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሲሻወርቅ ስጦታው እንዳሉት ፓርኩ በኢኮ-ቱሪዝምና በአየር ንብረት ለውጥ አገራዊ ፋይዳው የላቀ ነው፡፡

ይሁንና ፓርኩ በአሁኑ ወቅት በህገ-ወጥ ሰፈራ፣ ግብርና፣ የእንስሳት አደን፣ በደን ጭፍጨፋ እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ከተማ በሚወጣው ቆሻሻ አደጋ እንደተጋረጠበት ገልጸዋል፡፡

በእዚህም በፓርኩ ውስጥ ከሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት መካከል ከሰንቀሌ የመጡት 130 የስዌይን ቆርኬዎች ሙሉ በሙሉ የጠፉ ሲሆን የሜዳ ፍየል፣ የሜዳ አህያና የቆላ አጋዘን እንዲሁም ሌሎች የዱር እንስሳት ቁጥራቸው እየተመናመነ መምጣቱን አቶ ሲሻወርቅ ገልጸዋል፡፡

የደን ጭፍጨፋ ችግርን ለመቅረፍ ከአካባቢና ደን ጥበቃ፣ ከፍትህና ፀጥታ አካላት እንዲሁም በየደረጃው ካሉ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት መዋቅሮች ጋር የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት የችግሩ መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ በጋሞ ጎፋ ዞንና በኦሮሚያ ጉጂ ዞን የሚገኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፓርኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአደጋ ውስጥ ካሉ ፓርኮች ተርታ ሊመዘገብ የተቃረበ በመሆኑም ፓርኩን ለመታደግ የአመራር ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ስምኦን ሽብሩ በበኩላቸው፣ የፓርኩ መጥፋት በውስጡ ያሉ ብዝሃ ሕይወትና የአካባቢውን ማህበረሰብ እንደሚጎዳ ገልጸዋል።

በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም አስገንዝበዋል ፡፡

የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ሕልውናን አስመልክቶ በተከታታይ በተደረጉ ጥናቶችና ምርምሮች ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ከ10 ዓመታት ያላነሰ ውይይት ሲደረግ ቢቆይም እስካሁን ህልውናው ሊከበር ባለመቻሉ በአሁኑ ወቅት የአመራሩ ቁርጠኝነት ግድ እንደሚልም ጠቁመዋል ፡፡

የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ማሪዬ በበኩላቸው ፓርኩ በ514 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት በ1967 ዓ.ም ዕውቅና ተሰጥቶት ቢወከልም ከዚያ በኋላ በአስተዳደሩ ትኩረት ባለመሰጠቱ ለጉዳት መዳረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በፓርኩ እየተፈጸመ ያለው ህገ-ወጥ ሠፈራ፣ ግብርና፣ ግጦሽ፣ አደንና ደን ጭፍጨፋ አገሪቱ ያወጣቻቸውን የዱር እንስሳት ጥበቃ ህጎችና የብሔራዊ ፓርክ አስተዳደር ህጎችን በተግባር ለማዋል አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

እንደ አቶ አብርሃም ገለጻ፣ በፓርኩ ክልል እስከ 880 አርብቶ አደሮች የሚኖሩ ሲሆን በእዚህም ከ20 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት በፓርኩ ውስጥ ይሰማራሉ።

ፓርኩ ከጊዜ ወደጊዜ ለግብርናና ለግጦሽ አገልግሎት መዋያ እየሆነ መምጣቱ አብዛኛው የዱር እንስሳት እንዲሰደዱ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ በፓርኩ ሕልውና ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ትልቁ ማነቆ የወሰን ችግር በመሆኑ ዳግም ለመከለል ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የደቡብ ምዕራብ ቀጠና አስተባባሪ አቶ ገብረ መስቀል ግዛው እንደገለጹት ፓርኩ በኦሮሚያ ጉጂ ዞን በኩል ወሰኑ አለመከበሩን ተከትሎ አደጋ ላይ ሊወድቅ መቻሉን አስረድተዋል ፡፡

ችግሩን ለመፍታት የደቡብና የኦሮሚያ ክልልን ያሳተፈ ውሳኔ ለማስተላለፍ በአሁኑ ጊዜ ቅድመ ዝግጅት የተጠናቀቀ በመሆኑ በሚደረገው ዳግም ክለላ የፓርኩ ችግር በዘላቂነት ሊፈታ እንደሚችል አመለክተዋል።                                                

ፓርኩ በውስጡ ከ103 በላይ አጥቢ የዱር እንስሳት፣ 33 ተሳቢና ተራማጅ እንስሳት፣ 351 የአዕዋፍ ዝርያዎችና ከአንድ ሺህ በላይ የእፅዋት ዝሪያዎች መያዙን ፡፡

Last modified on Monday, 12 February 2018 15:53
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን