አርዕስተ ዜና

በዞኑ የደን ሃብት በወጣቶች እንዲጠበቅ መደረጉ የደን ጭፍጨፋ እንዲቀንስ ማድረጉ ተገለጸ

235 times

መተማ ሚያዚያ8/2010 በምዕራብ ጎንደር ዞን የተከለለ የተፈጥሮ ደን ሃብት በተደራጁ ወጣቶች እንዲጠበቅ መደረጉ ህገ-ወጥ የደን ጭፍጨፋ እንዲቀንስ ማስቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመመሪያው የአካባቢ፣ የደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ አድጎ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ በዞኑ በሚገኙ ቋራ፣ መተማና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች ሰፊ የተፈጥሮ ደኖች ይገኛሉ።

ቀደም ሲል በደን ሀብቱ በሞፈር ዘመት እርሻ፣ በሰደድ እሳት፣ በኢንቨስትመንት እንዲሁም ለቤት ግንባታ፣ ለክሰል ፍጆታና በመሳሰሉት ሲባል ሃገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች ላይ ከፍተኛ ውድመት ይደርስ እንደነበር አስታውሰዋል። 

ከእዚህ በተጨማሪ የእርሻ መሬት ለማጽዳት በሚል ይለቀቅ የነበረው የሰደድ እሳት በየዓመቱ ከ10 ሄክታር በላይ ደን ያወድም እንደነበረና በአሁኑ ወቅት በወጣቶቹ አማካኝነት ህገወጥ ተግባሩን መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል።

የደን ውድመቱን በዘላቂነት ለመከላከልም 202 ሺህ ሄክታር መሬት በጂፒኤስ በመለካትና የደን ማኔጅመንት ዕቅድ እንዲዘጋጀለት መደረጉን ተናግረዋል።

በተከለለው የደን መሬት ውስጥ በ36 ማህበራት የተደራጁ ከ6 ሺህ በላይ ወጣቶች ከ179 ሺህ ሄክታር በላይ ደን ተረክበው ከደን ሃብቱ እየተጠቀሙ ውድመቱን በመከላከል ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

"ወጣቶቹ በእንስሳት እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በእጣንና ሙጫ እንዲሁም በቁማቸው የደረቁ ዛፎችን ሸጠው እንዲጠቀሙ በማድረግ የተፈጥሮ ደኑን እንዲጠብቁ ስልት ተነድፎ መተግበሩ ውጤታማ እያደረገ ነው" ብለዋል።

በመተማ ወረዳ ሌንጫ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት በየነ አለሙ ቀደም ሲል በአካባቢው የደን ውድመት እንደነበር አስታውሶ በአሁኑ ወቅት ደኑ ለአየር ንብረት ለውጥ ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆኑ ከፍተኛ እንክብካቤ እያደረጉለት መሆኑን ተናግሯል።

” ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ የዕጣንና ሙጫ ዛፎችን ያለአግባብ ስንጠቀም ነበር፤ አሁን በተፈጠረልን ግንዛቤ ዛፎቹን ሳንጎዳ በትክክለኛ መንገድ እየተጠቀምን እንገኛለን " ብሏል፡፡

በተከታታይ በሚያደርጉት ክትትልና ጥበቃም የደን ሃብቱን ካለአግባብ የሚጠቀሙ አካላት ሲኖሩ በመምከር ከህገ ወጥ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስረድቷል።

በማህበራቸው አማካይነት የደን ጥበቃ ሥራ እንደሚሰሩና ጉዳት ያደረሱ አካላትም በህግ ተጠያቂ እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የመተማ ወረዳ የአባት አርበኞች ተጠሪ አቶ በቀለ ጀምበር ናቸው፡፡

በመተማ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ጀጃው አብርሃ በእርሻ መሬታቸው ዙሪያ የሚገኙ የተፈጥሮ ደኖችን በመጠበቅ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል ከእውቀትና ግንዛቤ ጉድለት በደን ሃብቱ ላይ ጉዳት ይደርስ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ህገ ወጥ ተግባሩ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተዋል።

በአካባቢው በክልሉ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ጥናት ተደርጎባቸው በጥብቅ ስፍራዎች የተያዙ የማህበረ ስላሴ አንድነት ገዳም፣ የጎደቤ ጥብቅ ደንና የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ  ደኖች ይገኛሉ።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን