አርዕስተ ዜና

በምሥራቅ ወለጋ ከ113ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተከናወነ

284 times

ነቀምቴ ሚያዚያ 6/2010 በምሥራቅ ወለጋ ዞን በተያዘው ዓመት የበጋ ወራት  ከ113ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ተፋሰስን መሰረት ያደረገ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑ ተገለጸ፡፡

የዞኑ የእርሻ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት እንዳመለከተው ስራው የተከናወነው ከጥር አጋማሽ 2010ዓ.ም  ጀምሮ በ237 የገጠር ቀበሌዎች በተመረጡ 279 ንኡስ ተፋሰሶች ውስጥ ነው፡፡

ቀበሌዎቹ  በዞኑ 17 ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆን ከተከናወኑት ስራዎች መካከል የእርከን፣የጎርፍ ማፍሰሻና መቀልበሻ ቦዮች፣ እርጥበትን የሚያቁሩና የተለያዩ የክትር ተግባራት ይገኙበታል፡፡

36ሺህ102 ሄክታር መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ተከልሏል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እንክብካቤና አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ጌታሁን ምናሴ እንዳሉት በስራው ከ298ሺህ በላይ  አርሶ አደሮች ለ35 ቀናት ነጻ የጉልበት አስተዋጽኦ አድርገዋል፤  አስተዋጽቸው በገንዘብ ሲተመንም  ከ187 ሚሊዮን ብር እንደሚበልጥ ይገመታል፡፡

ከአርሶ አደሮቹ መካከል በዋዩ ቱቃ ወረዳ የጉቴ የገጠር ቀበሌ  ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ዱጉማ በሰጡት አስተያየት በግብርና ባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ሙያዊ ድጋፍ በመታገዝ ባላቸው አምስት  ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በማሳቸው ላይ የአፈርን ለምነት የሚጠብቁ የተለያዩ ችግኞችን መትከላቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ቀደም ብሎ ባከናወኑት ተመሳሳይ ስራ የአፈር ለምነት ተጠብቆ  ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንደረዳቸው ያመለከቱት አርሶ አደሩ የእንስሳት መኖ በማልማት ከብት እያደለቡ ገቢያቸውን ለመጨመር ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸውም ገልጸዋል፡፡

የዚህ ቀበሌ አርሶ አደር ፍቃዱ ብርሃኑ በበኩላቸው" የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከመጀመሩ በፊት አፈሩ በየዓመቱ በጎርፍ እየተሸረሸረ ለም አፈሩ በመሟጠጡ በምግብ እህል ራስን ያለመቻል ሁኔታዎች ነበሩ"  ብለዋል፡፡

ለም አፈሩ እንዳይጠረግ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በየዓመቱ በማሳቸው ላይ በመስራታቸው  የነበረው ችግር እየተፈታ ምርታማነት ለመጨመር እዳገዛቸው ተናግረዋል፡፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን  ባለፉት ሰባት ዓመታት 887ሺህ 452 ሄክታር የተጎዳ መልማቱንና  ከ179ሺህ ሄክታር በላይ ደግሞ  ከሰውና እንስሳት ንክኪ ተከልሏል፡፡

በዚህም   ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ የሚመጣ ከመሆኑም በላይ  ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች በሰው ሰራሽ ደን እየተሸፈኑና የመሬቱም ለምነት እየጨመረ መምጣቱን የዞኑ የእርሻ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን