አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያ ደን ልማት ስራ በሳይንሳዊ መንገድ እየተካሄደ አይደለም-ምሁራን

441 times

አዲስ አበባ ሚያዚያ 4/2010 በኢትዮጵያ የደን ልማት ስራ በሳይንሳዊ መንገድ እየተካሄደ አለመሆኑን የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።

የኢትዮጵያ የደን ባለሙያዎች ማህበር 5ኛ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ሲሆን በሀገሪቱ እየተከናወነ የሚገኘው የደን ልማት ስራ በአብዛኛው በጥናት ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን በመድረኩ ይፋ አድርጓል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አለሙ ገዛኸኝ እንደተናገሩት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ቢተከሉም የአካባቢ ተስማሚነት ጥናት ባለመካሄዱና ክትትልና ጥበቃ ስለማይደረግላቸው አብዛኞቹ ሳይፀድቁ ቀርተዋል።

ማህበሩ ችግሩን ለመቀነስ ከአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገርና ጥናቶችን በማካሄድ ሳይንሳዊ የደን ልማት አካሄዶችን ተግባር ላይ ለማዋል እየሰራ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።

የደን ልማት ባለሙያዉ ዶክተር ሙሉጌታ ልመንህ እንዳሉት በኢትዮጵያ ደን የሚገኝባቸው አካባቢዎች እየተመናመኑ በመምጣታቸው አለም አቀፍ በሆኑ የዘርፉ ሳይንሳዊ መመዘኛዎች ደን አለ ብሎ ለመናገር ያስቸግራል ።

ኢትዮጵያ ደን ማልማት የሚያስችል ምቹ መልክአ ምድር ቢኖራትም የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ከመሳሰሉ ለደን ልማት ምቹ ካልሆኑ ሀገራት ሳይቀር የደን ውጤቶችን በከፍተኛ ወጭ ወደ ሀገር ውስጥ እንደምታስገባም ተናግረዋል።

የደን ሀብት የሀገርን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ትልቅ አቅም ቢኖረውም በኢትዮዽያ ያለው ድርሻ ከአራት በመቶ በታች መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የደን ልማት ባለሙያው ዶክተር ተፈራ መንግስቱ ናቸው።

በቂ የደን ዘር አለመኖር ፣ ለደን ልማት ተስማሚነት ጥናት አለመደረግ ፣ በሳይንስ ያልተደገፈ የችግኝ ተከላና  የደን ባለቤትነት መብት ጉዳይ በሀገሪቱ ደን በከፍተኛ መጠን እንዳይለማ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ለደን ልማት የሚመድበው በጀት አነስተኛ በመሆኑ ቢስተካከል ፣የግል ባለሀብቶች በደን ልማት እንዲሰማሩ ቢደረግ እንዲሁም ከችግኝ ተከላ በኋላ ጠበቅ ያለ የደን ጥበቃ እንዲኖር ባለሙያዎቹ በመፍትሔነት አስቀምጠዋል።

የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዱ ዳሌ በበኩላቸው በኢትዮዽያ አሁን ያለውን የ15 ነጥብ 5 በመቶ የደን ሽፋን ለማሳደግ አዋጅ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ 1065 ደን ከመልማቱ አስቀድሞ የባለቤትነት መብት፣ የሚለማው ደን በአካባቢው የሚኖረው ተስማሚነትና ጠቀሜታ እንዲሁም በመደበኛነት ክትትልና እንክብካቤ የሚያደርግ አካል እንዲኖር ያስገድዳል ብለዋል።

የሚለሙት ደኖች ከሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በላይ የአካባቢ መራቆትን የሚያስቀሩ፣ በረሃማነት እንዳይስፋፋ የሚያደርጉ ፣  የስርዓተ ምህዳርን ጤንነትን የሚጠብቁና ከውጭ ሀገር የሚገቡ የደን ውጤቶችን የሚተኩ እንዲሆኑ በፀደቀው አዋጅ መካተቱን ሚንስትሩ ገልፀዋል።

ከምንም በላይ ደን ሲለማ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚና አሳታፊ በማድረግም የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።

 

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን