አርዕስተ ዜና

ውጤታማ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ለማከናወን ልዩ ትኩረት ማድረጋቸውን ሦስት ክልሎች ገለፁ

12 Jan 2018
468 times

አዳማ ጥር 4/2010 ዘንድሮ የሚካሄደውን የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ በተሻለ ውጤታማነት ለማስፈጸም ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የኦሮሚያ፣ ጋምቤላና ደቡብ ክልሎች ገለጹ።

የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የተፋሰስ ልማትና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ እንዳስታወቁት ዘንድሮ የሚካሄደውን የተፋሰስ ልማት በክልሉ በተሻለ ሁኔታ ለማከናወን ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

ለእዚህም ወደሥራ ከመገባቱ በፊት በየደረጃው ከሚገኙ የአመራር አካላትና ከሕዝቡ ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉንና የክህሎት ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል።

ለልማት ሥራው አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ፈጻሚ አካላትን ዝግጁ የማድረግ ሥራ ቀደም ብሎ መጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

" ነባሩን የኦሮሞ ሕዝብ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ፣ እሴትና ባህል ለዘላቂ ልማት ንቅናቄ በሚል መርህ" በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እንቅስቃሴው መጀመሩንም አመልክተዋል።

አቶ ስለሺ እንዳሉት፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራው 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።

በዘመቻ መልክ ለአንድ ወር ከሚከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል የተለያዩ የስነ አካላዊ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች፣ 890 ሺህ ኪሎ ሜትር የእርከን  ሥራ ይገኙበታል።

ከእዚህ በተጨማሪ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የውሃ ማስወገጃ እስተራክቸር፣ የእርጥበት ማቆያ፣ 514 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከሰውና ከእንሰሳት ንኪኪ ውጭ ማድረግና ሌሎችም በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን መታቀዱንም አስረድተዋል።

የጋምቤላ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ተወካይ አቶ ኬት ቾል በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ የዘንድሮውን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ደረጃ ማከናወን እንዲቻል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

በ2010 በጀት ዓመት 538 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ አዳዲስ የሥነ-አካላዊ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ለማከሄድ ዕቅድ መያዙን ጠቁመው፣ በተያዘው ጥር ወር በአምስት ወረዳዎች የተለየዩ የህዝብ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል። 

ሥራውን ለማስፈጸም 198 ሺህ የተለዩ የቅየሳና የእጅ መሳሪያዎች መዘጋጀታቸውንም አቶ ኬት ገልጸዋል።

በደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ቦጋለ ሌንጮ በበኩላቸው የተፋሰስ ልማትን አስመልክቶ ለተሳታፊዎችና አመራር አካላት ቀደም ብሎ ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል።

በክልሉ በሚከናወነው የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ በጉልበት የሚሳተፍ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሰው ኃይል  መለየቱንም አመልክተዋል።

ከዓመት ዓመት የሚሰሩ ሥራዎች እየተሻሻሉ ቢመጡም የጥራት፣ ልቅ ግጦሽ እንዲሁም የተሰሩ ሥራዎች  መረጃ አያያዝ ላይ ውስንነቶች እንደነበሩ ገልጸው፣ ዘንድሮ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከናወኑ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራዎች ከጥቅም ውጪ ሆነው የነበሩ ተራሮች፣ የእርሻ፣ የደንና የግጦሽ መሬቶች አገግመው ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል።

የከርሰ ምድር ውሃ፣ የአፈር ለምነትና በመስኖ የሚለማው መሬት የጨመረ ሲሆን የአፈር መሸርሸር መጠን ዝቅ ማለቱም ተመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪ በመኖ አቅርቦት፣ በማር ምርት መጨመር፣ በሴቶች ተጠቃሚነት፣ በድህነት ቅነሳና በምግብ ዋስትና ላይ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ነው።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ