አርዕስተ ዜና

የተቀናጀ የስነ ምህዳር ጥበቃና የመሬት ልማት አስተዳደር ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ ነው--- ሚኒስቴሩ

12 Jan 2018
584 times

አዳማ ጥር 4/2010 ህብረተሰብ አቀፍ የተቀናጀ የስነ ምህዳር ጥበቃና የመሬት ልማት አስተዳደር ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ የአካባቢ ደን ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ ዘላቂ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር ተስፋዬ ኃይሌ እንዳሉት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ከዳር ለማድረስ ነው፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማ የብዝሃ ህይወት ሃብቱ በሀገሪቱ የልማት ዕድገት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖረውና የተጀመረው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ህብረተሰቡን በንቃት በማሳተፍ ዘላቂ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ነው።

የሀገሪቱን ምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥም  ያግዛል።

ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ፣አማራ፣ደቡብ፣ትግራይ፣ሶማሌና አፋር ክልሎች በሚገኙና በምግብ እጥረት በተጎዱ 12 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ከ2010 ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ነው።

ለፕሮጀክቱ ማካሄጃ  ከተባበሩት መንግስታት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ፕሮግራም 11 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ መደረጉን ያመለከቱት ባለሙያው " ከህዝብና ከመንግስት 144 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የቁሳቁስ ፣የጉልበትና የዕውቀት ተሳትፎ ይደረጋል "ብለዋል።

እስከ 2014 የሚቆየው ፕሮጄክቱ ከ220 ሺህ በላይ ቤተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ከዶክተር ተስፋዬ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

በዚህም የእንስሳት መኖ ልማት፣ንብ ማነብ፣በአፈርና ውሃ ዕቀባ፣በደን ልማት፣በአካባቢ ጥበቃና ተያያዥ መስኮች ከ140ሺህ በላይ ወጣቶች ጨምሮ ሌሎችም የህብረተሰብ  ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የብዝሃ ህይወት ሃብቱ በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ለማስቻል የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለብዝሃ ህይወት ሀብት ልማት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በሁሉም ወረዳዎች ለማስፋፋትም  የደንና አካባቢ ሚኒስቴር፣  የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙም ተመልክቷል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ