አርዕስተ ዜና

በግራር ጃርሶ ወረዳ ተራቁቶ የነበረ 33 ሺህ ሄክታር መሬት መልሶ አገግሟል

12 Jan 2018
441 times

ፍቼ ጥር 4/2010 በኦሮሚያ  ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ ተራቁቶ የነበረ 33 ሺህ ሄክታር መሬት በአርሶ አደሮች ጉልበት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ለአገልግሎት መብቃቱን የወረዳው አስተደደር አስታወቀ ።

በሁለ ገብ የተቀናጀ ልማት  የጎላ አስተዋጽኦ  ላበረከቱ 88 አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች በግራር ጃርሶ ወረዳ  ጊኖ ቀበሌ ዛሬ  በተከናወነው ስነ ስርዓት  ተሸልመዋል።

የግራር ጃርሶ ወረዳ  አስተዳዳሪ  አቶ ዳንኤል ሰብስቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በወረዳው ለብዙ   ዓመታት እፅዋት  አልባ በመሆን ተራቁቶ በነበረው  መሬት 29 ሺህ አርሶአደሮች የተሳተፉበት የመልሶ ማልማት ስራ ሲካሄድ  ቆይቷል፡፡

አርሶ አደሮቹ በተፋሰስ ልማት ፣በእርከንና በሌሎችም አዳዲስ የአሰራር ዘዴዎች  ለአምሰት ዓመታት ባደረጉት ርብርብ  መልሶ እንዲያገግምና  ጥቅም እንዲሰጥ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የተቦረቦሩ  አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋምና ከጥቅም  ውጭ የሆነ የወንዝ ዳር  መሬት  ደግሞ በመስኖ በማልማት ምርት እንዲሰጥ አርሶ አደሮቹ አመቻችተዋል።

በተለይ የተራቆቱ አካባቢዎችን ከሰውና እንሰሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ የሳርና የማገዶ ተክሎችን በመዝራት ያካሄዱት ልማት ውጤታማ መሆኑን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

በሰብልና ፍራፍሬ ምርታማነት  የሚታወቁት የወረዳው አርሶ አደሮች በአሁኑ ወቅትም በአዳዲስ አደረጃጀቶች  በመካተት የአካባቢያቸው የተፈጥሮ ሃብት   እንዳይጎዳ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን  አጠናክረው ለመስራት አቅደው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡

የወረዳው አርሶ አደሮች  የምግብ ዋስትናቸውን  ለማረጋገጥ በግልና በጋራ ከሚያካሂዱት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራም  ተጨማሪ የገቢ ምንጭ  እያገኙ መሆኑን አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

ለአርሶአደሮቹ  የተዘጋጀው የእውቅና ሽልማት ልቅ ግጦሽና የደን ጭፍጨፋን  በመከላከል፣ ቦረቦር መሬትን በማዳን ፣በምንጭ ማጎልበትና በሌሎች  የተቀናጀ የግብርና ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማበረታታ መሆኑን የወረዳው አስተዳዳሪ አስታውቀዋል።

ከወረዳው አርሶ አደሮች መካከል የጊኖ ቀበሌ ተሸላሚ አቶ ሙሰማ አበራ በሰጡት አስተያየት  የግብርና ባለሙያዎች በሚሰጧቸው  ምክር በመታገዝ  ደን ያለ አግባብ  እንዳይመነጠር የድርሻቸውን እየተወጡ  እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሌላው የወርጡ ቀበሌ ተሸላሚ አርሶ አደር ቤኩማ ካሳ  ውሃን በማሰባሰብ ፣ምንጭ በማጎልበትና ሌሎች አዳዲስ የምርት ማሳደጊያ ዘዴዎች  በመጠቀም ግንባር ቀደም በመሆናቸው ለሽልማት እንደበቁ ገልጸዋል፡፡

ይህንን ስራ አጠናክረው በመቀጠል የተሻለ  ገቢ እንዲኖራቸው ከግብርና ባለሙያዎችና አመራሮች ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ  ጠቁመው ሌሎችም በተመሳሳይ መልኩ ቢሰሩ የጋራ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ አመልክተዋል ።  

በሁለገብ የተቀናጀ የግብርና ልማት የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ በወረዳው 21 ቀበሌዎች የሚገኙ  አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች የምሰክር ወረቀት፣ ለእርሻ ስራና ለቤት ውስጥ መገልገያ  የሚውሉ  መሳሪያዎች ተሸልመዋል፡፡

ሽልማቱን ያበረከቱት የዞኑና የወረዳው አስተዳደሮች እንዲሁም አክሽን ኤይድ የተባለው የተራድኦ ድርጅት በጋራ በመሆን ነው፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ