አርዕስተ ዜና

ታንዛንያ የደን ሀብቷን ለመታደግ ከሰል ጥቅም ላይ እንዳይውል ልታደርግ ነው

12 Jan 2018
270 times

ጥር 3/2010 የታንዛንያ መንግሥት እኤአ በ2025 ከሰል ጥቅም ላይ እንዳይውል ለማድረግ  የከሰል ምርት ለውጭ ገበያ እንዳይላክ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

እንደ ዳሬሰላም ባሉ ከተሞች ርካሽ የሃይል ፍላጎትን ለማሟላት ከሰል አክሳዮችና ነጋዴዎች እጸዋትን በፍጥነት እየጨፈጨፉ መሆናቸው ሀገሪቱ በመቶሺዎች በሚቆጠር ሄክታር መሬት ላይ የነበረ የደን ሃብቷን እንድታጣ አድርጓታል፡፡

ከሀገሪቱ ኢነርጂና ሚኒራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው  የሀገሪቱ መዲና ዳሬሰላም ብቻ በየዕለቱ አንድ ሺህ የኳስ ሜዳዎችን ያህል ስፋት ባለው ቦታ ላይ ያሉ ዛፎችን ታወድማለች፡፡

በቅርቡ በመንግሥት የተጣለው ዕገዳ ከሰል እኤአ በ2025  ጥቅም ላይ እንዳይውል ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ነው የቻይናው ዓለም ዓቀፍ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ በድረገጹ ያስነበበው፡፡

የከሰል ነጋዴዎች መንግሥት በአንድ ኩንታል ከሰል ላይ የሚጥልባቸው ግብር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ለከሰል ምርት የሚያገለግሉ ዛፎችም አነስተኛ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፡፡

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከከሰል ፍጆታ ጋር በተያያዘ ታንዛንያን የሚስተካከላት የለም፡፡ ሀገሪቱ በየዓመቱ 2 ሚሊዮን ቶን ከሰል ጥቅም ላይ ታውላለች፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ግማሽ ያህሉን የምትጠቀመው መዲናዋ ዳሬሰላም ነች፡፡

የከሰል ፍጆታዋ የደን ሃብቷን ክፉኛ ቢያመናምንባትም የሀገሪቱ የከሰል ምርት ፍላጎት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

በከሰል የሚሰሩ የምግብ ማብሰያዎች ጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩ ትውልድ ተሻግረዋል፡፡  ይሁን እንጂ ከሰልን ጥቅም ላይ ማዋል በአካባቢ ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ በተመለከተ የተሰሩ የግንዛቤ ማጎልበቻ ስራዎች አማራጭ የኃይል ምንጮች  ትኩረት እንዲያገኙ ማድረጋቸው ተመልክቷል፡፡

የዓለም ባንክ ሀገሪቱ በየዓመቱ ከከሰል 650 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደምታገኝ ቢገልጽም መንግስት ግን አማራጭ የኃይል ዘርፎችን በማስፋት የደን ሃብቱን ለመታደግ እየሰራ ነው፡፡

የተወሰኑ አምራቾችም ከሰጋቱራና መሰል የእንጨት ቁርጥራጮች  አዲስ ከሰል ማምረት መጀመራቸው በዘገባው ተመልክቷል፡፡

ይህን መሰል ምርት ለባህላዊ ከሰል ምርት ዘላቂነት ያለው ምላሽ የሚሰጥ ቢሆንም የህብረተሰቡን አመለካከት ለመቀየር ግን ጊዜ መውሰዱ እይቀርም ተብሏል፡፡

መንግሥት የጋዝን ዋጋ በመቀነስ፣ በከሰል አምራቾች ላይ የሚጥለውን ግብር በማሳደግና በከሰል ንግድ ላይ ቅጣቶችን በመጣል የሚወስዳቸው እርምጃዎች ንጹህና ቀጣይነት ያለው አካባቢን ለመፍጠር እንደሚያግዘው ተመልክቷል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ