አርዕስተ ዜና

በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል

10 Jan 2018
306 times

ባህር ዳር ጥር 2/2010 በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከተያዘው ወር አጋማሽ ጀምሮ በተለዩ ከ300 በሚበልጡ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን  ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።

በተለዩ ተፋሰሶች ዘጠኝ ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው  በአርሶ አደሩ ተሳትፎ  ይከናወናል።

በመምሪያው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዳኛው አምሳሉ ለኢዜአ እንዳሉት የማሳ ላይ ዕርከን፣ የተራቆተ መሬትን ከልሎ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ የመጠበቅ ተግባር ከሚከናወኑት ስራዎች ይገኙበታል።

ከተያዘው ወር አጋማሽ ጀምሮ ለ30 የስራ ቀናት በሚቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የሚሳተፍ ከ218 ሺህ በላይ የሰው ኃይል ተለይቶ  ተዘጋጅቷል።

በአሁኑ ወቅትም ከዞን  እስከ ቀበሌ ድረስ ለሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና ለአርሶ አደሮች የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የንቅናቄ መድረኮች እየተካሄደ ይገኛል።

አስተባባሪው እንዳመለከቱት በዞኑ ባለፉት ሰባት ዓመታት በህዝቡ የተደራጀ ንቅናቄ በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ 310 ሺህ ሄክታር የተራቆተ መሬት በደን እንዲለብስ ተደርጓል።

ተፋሰሶቹ በማገገማቸው አርሶ አደሩ ለእንስሳት  ዋነኛ የመኖ መገኛ ምንጭ ሆኖ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

የተጎዳው አካባቢ በመልማቱና ደርቀው  የነበሩ ምንጮች እንደገና በመመለሳቸው ለመስኖ ልማት፣ ለንብ ማነብ፣ ለእንስሳት እርባታና ማድለብ ስራ አመቺ ሁኔታ መፈጠሩም ተመልክቷል፡፡

" የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የሚያስገኘውን ጥቅም ጠንቅቀን መረዳታችን ለስራው ይበልጥ እንድንዘጋጅ አድርጎናል"  ያሉት ደግሞ የባንጃ ወረዳ አርሶ አደር አበራ ተስፋዬ ናቸው።

ባለፉት ዓመታት ተፈጻሚ በሆነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራም የተጎዳ ቦረቦራማ መሬት እንዲያገግምና  የእርሻ መሬታቸውም  የአፈር ለምነት እየተሻሻለ እንዲመጣ ያገዛቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቅርቡ በሚጀመረው ተመሳሳይ የልማት ስራም እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም የቀበሌው አርሶ አደር ለመሳተፍ ተዘጋጅተው እየተጠባበቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ