አርዕስተ ዜና

በደቡብ ክልል የሀገረሰብ ነባር የሰብል ዝርያዎችን ጠብቆ ለማቆየት እየተሰራ ነው

03 Jan 2018
442 times

ዲላ ታህሳስ 25/2010 በደቡብ ክልል የሀገረሰብ ነባር የሰብል ዝርያዎችን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የአካባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን ገለፀ፡፡

በጌዴኦ ዞን የቡሌ ወረዳ አርሶ አደሮች ሀገር በቀል ዝርያዎችን ጠብቆ ለማቆየት በማህበር ተደራጅተው እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራት በክልሉ የሥራ ኃላፊዎችና ከተለያዩ ዞኖች በመጡ አርሶ አደሮች ተጎብኝቷል ፡፡

በመስክ ጉብኝቱ ላይ የተገኙት በደቡብ ክልል አካባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን የብዝሀ-ሕይወት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ባፋ እንደገለፁት፣ በሀገሪቱ ከዚህ በፊት በየአካባቢው ይመረቱ የነበሩና አሁን ላይ ለመጥፋት የተቃረቡ በርካታ ሀገር በቀል ሰብሎችና የእፅዋት ዝርያዎች አሉ፡፡

"ዝርያዎቹ ከምግብነት ባለፈ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ሲሆን በሽታና የአየር ፀባይ መዛባትን የመቋቋም እንዲሁም አካባቢን የመላመድ አቅም አላቸው" ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዝርያዎቹ ሳይጠፉ ለመንከባከብና ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል ፡፡

አቶ መላኩ እንዳሉት፣ እስካሁን በክልሉ ሰባት የአርሶ አደሮች የሀገረሰብ ነባር ሰብል ጥበቃና የዘር ባንክ ማህበራት ተቋቁመው አርሶ አደሩ በራሱና በማህበሩ ማሳ ላይ ዝርያዎቹን እንዲያመርትና ለሌሎች እንዲያስተላልፍ ጥረት እየተደረገ ነው ፡፡

ጉብኝቱ በጋሞጎፋ፣ ስልጤ እና ጉራጌ ዞኖች እየተቋቋሙ ላሉ ተጨማሪ የአርሶአደሮች የሀገረሰብ ነባር ሰብል ጥበቃና የዘር ባንክ ማህበራት ግብአት እንዲሆንና አርሶ አደሮቹ ልምድ እንዲቀስሙ ታስቦ መካሄዱን አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡

በጌዴኦ ዞን የአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽሕፈት ቤት የብዝሀ-ሕይወት ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ሞገስ ተሰማ የማህበሩ አባል የሆኑ አርሶ አደሮች ምርታማነትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጽህፈት ቤቱ በመስመር የአስተራረስ ዘዴና በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል፡፡

በቡሌ ወረዳ የሆርሲንሶ የነባር ሰብል ጥበቃና አምራች መሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ አርሶ አደር ከበደ አዱላ፣ ማህበሩ በ2005 ዓ.ም 50 አባል አርሶ አደሮች መመስረቱንና በአሁኑ ወቅት የአባላቱ ቁጥር 139 መድረሱን ተናግረዋል ፡፡

"ማህበሩ በአሁን ወቅት 42 ነባር የሀገረሰብ ሰብል ዝርያዎችን በማሰባሰብ በአርሶ አደሩና በማህበሩ ማሳ ለይ እያመረተ ይገኛል" ብለዋል።

አባላቱ ለዘር የሚወስዱትን ሰብል 20 በመቶ ወለዱን ጨምረው በምርት ማሰባሰብ ወቅት ለማህበሩ እንደሚመልሱም አመልክተዋል።

ማህበሩ በዘር ወቅት ለአባላቱ አሰራጭቶ የሚሰበስበውን ጨምሮ በዓመት ከ43 ኩንታል በላይ የሰብል ዘሮችን ወደ ዘር ባንኩ እንደሚያስገባም አስረድተዋል ፡፡

ከስልጤ ዞን ዳሎቻ ወረዳ የመጡት አርሶ አደር ሸረፋ ላሉቴ በበኩላቸው በወረዳቸው ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን አዲስ የነባረ ሀገር በቀል ሰብል ጥበቃ ማህበር እያቋቋሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"በጉብኝቱ የቀሰምኩትን ልምድ በአካባቢዬ ለመተግበር ተዘጋጅቻለሁ" ብለዋል ፡፡ 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ