አርዕስተ ዜና

መገናኛ ብዙሃንና የኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ የሃሪቱን ብዝሃ ህይወት ሊያስተዋወቁ ይገባል...ዶክተር ነገሬ ሌንጮ

02 Jan 2018
489 times

ጋምቤላ ታህሳስ 24/2010 መገናኛ ብዙሃንና የኮሚውኑኬሽን ዘርፉ የሀገሪቱን ብዝሃ ሕይወት በማስተዋወቅ በኩል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዶክተር ነገሬ ሌንጮ አስታወቁ።

የማጃንግ ደን በአለም የከባቢ ህይወት ጥብቅ ስፍራነት /ባዮስፊር ሪዘርቭ/መመዝገቡን አስመልክቶ በማጃንግ ዞን ሜጢ ከተማ በተካሔደ አውደ ጥናት ላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ሃገሪቱ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት ብትሆንም በዘርፉ ብዙም አልተሰራበትም።

የሚታየውን የመረጃ ተደራሽነት ክፍተት በማሳደግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነቷን እንድታሳድግ በማስተዋወቅ በኩል የመገናኛ ብዙሃንና ኮሚኒኬሽን ዘርፉ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የሚገኙ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ሀብቶችን በመንከባከብ በኩል ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው የማጃንግ ደን በሀገራችን አምስተኛው የአለም የከባቢ ህይወት ጥብቅ ስፍራ ሆኖ መመዝገቡ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

ደኑ በተለይም ከቱሪዝም መስህብነት ባለፈ ለሀገሪቱ ብሎም ለአለም የከባቢ አየር ለውጥ የሚያበረክተው አስተዋፆኦ ከፍተኛ እንደመሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትና የአካባቢው ማህብረሰብ ሊንከባከበው እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው "ሀገሪቱ የጀመረችውን ልማት ለማሳካት በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር የታገዙ ሥራዎች ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።

ለስኬታማነቱም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይም የአካባቢያቸውን የብዝሃ ህይወትና ስነ-ምህዳር መሰረት ያደረጉ ሥራዎችን በጥናትና ምርምር ውስጥ በማካተት ማህብረሰቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሚኒስትር መሰሪያ ቤቱ በተለይም በሀገሪቱ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለሚያከናውኑ ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይስና የባህል ድርጅት/ዩኔሴኮ/የከባቢ ህይወት ጥብቅ ስፍራነት የተመዘገበው የደኑ ብዝሃ ህይወት ተጠብቆ እንዲቆይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣የአካባቢው ማህብረሰብና አመራሮች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጋትለዋክ ቱት በበኩላቸው  የክልሉ መንግስት የአካባቢውን ብዝሃ ህይወት በማስጠበቅ የማህብረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል።

የማጃንግ ደን የከባቢ ህይወት ጥብቅ ስፍራ ሆኖ የተመዘገበው ከያዮ፡ከሸካ፡ከከፋ ደኖችና ከጣና ሐይቅ ቀጥሎ በኢትዮጵያ አምስተኛ በአለም ደግሞ 669ኛ በመሆን ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ