አርዕስተ ዜና

በጋምቤላ ክልል የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል

02 Jan 2018
408 times

ጋምቤላ ታህሳስ 24/2010 በጋምቤላ ክልል የአየር መዛባትና የአካባቢ መራቆት ችግሮችን ለመከላከል በክረምቱ ወራት የተጀመሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች በበጋው ወቅት ተጠናክሮ መቀጠላቸውን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን በጎበኙበት ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የአየር መዛባትና የአካባቢ መራቆት ችግሮችን ለመከላከል በክረምት የተጀመረው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ በበጋው ወራትም ተጠናክረው ቀጥሏል።

"በተለይም የበጋውን ሞቃታማ የአየር ጸባይ ተከትሎ ህብረተሰቡ የእርሻ ማሳውን ለማስፋት፣ አዲስ የግጦሽ ሳር ለማግኘትና ሌሎች ፍላጎቶቹን ለማሟላት የደን ጭፍጨፋና ቃጠሎ እንዳያደርስ በትኩረት እየሰራ ነው" ብለዋል።

በክልሉ ባለፈው ክረምት በ1ሺህ 420 ሄክታር መሬት ላይ የተተከሉ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የቡና፣ የፍራፍሬና የጥላ ዛፍ ችግኞች ከጉዳት ለመጠበቅ የአረም፣ የኩትኳቶና የሰደድ እሳት መካላከያ መስመር እየተሰራላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በዘላቂ የመሬት አያየዝ ፕሮጀክት በስድስት  ወረዳዎች ህዝቡን ያሳተፈ የተፋሰስና ደን ልማት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በፕሮጀክቱ ባለፉት ዓመታት በወረዳዎቹ በተከናወኑ የተፋሰስና የደን ልማትና ጥበቃ ስራዎች በርካታ የተራቆቱ አካባቢዎች ወደ ቀድሞው ስነ-ምህዳር ይዞታችው ተመልሰዋል" ብለዋል።

አርሶ አደሩ ባገገሙ መሬቶች ላይ ቡናን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የፍራፍሬና ሌሎች ቋሚ ተክሎችን በማልማት ስነ- ምህዳራቸው በዘለቄታው እንዲጠበቅ በማድረግ ውጤታማና ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆኑ ተግባራትን ማከናወኑን ገልፀዋል።

በቢሮው የፕሮጀክቱ አሰተባበሪ አቶ ሙላት ቢረጋ በበኩላቸው በፕሮጀክቱ ዘንድሮ እየለማ ያለውን ጨምሮ ባለፉት ስምንት ዓመታት በ75 ሺህ ሄክታር ምርት አልባ በሆኑ የአርሶ አደሩ ማሳዎችና የተራቆተ መሬት ላይ የተፋሰስ፣ የአፈር እቀባና የደን ልማትና ጥበቃ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ቡናን ጨምሮ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን በማቅረብ ማሳዎቻቸውን በገቢ አዋጪነት ባላቸው ቋሚ ተክሎችና የከብት መኖ ሳር አልምተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል" ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የታቀፉ ወረዳዎችን ቁጥር ከስድስት ወደ አስር በማሳደግ በቀጠዮቹ ሰባት ዓመታት ተመሳሳይ ስራዎች እንደሚከናው አመላክተዋል።

በማጃንግ ዞን ጎደሬ ወረዳ የመካከለኛው ሜጢ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ውበቱ ደረሰ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ማሳቸው በውሃ ታጥቦ ምርት አልባ ሆኖባቸው ነበረ።

ባለፉት አመታት ባካሄዱት የአፈርና ውሀ  ጥበቃ ስራ ማሳቸው በማገገሙ ቡና ተክለው በማልማት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ገልፀዋል።

ሌላው የዚሁ ወረዳ የዱሺ ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አደር ጋሻው ወርቅነህ ቀደም ሲል ለከብቶቻቸው የመኖ ሳር በማጣት ሲቸገሩ እንደነበር አስታውሰው "በአሁኑ ወቀት ተራቁቶ በነበረው መሬቴ ላይ ሮዳስ የተባለ ሳር በማልማት ለከብቶቼ በቂ መኖ ማግኘት ችያለሁ" ብለዋል።

በክልሉ ማጃንግ ዞን መንጌሽና ጎደሬ  ወረዳዎች የተካሄዱ የተፋሰስ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋት ሰሞኑን በዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጉብኝት ተካሂዷል።

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ