አርዕስተ ዜና

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም የተቀናጀ ቆሻሻ አጠቃቀም ፕሮጀክት ተግባራዊ ይደረጋል

01 Jan 2018
419 times

አዲስ አበባ  ታህሳስ  23/2010  ከተያዘው ዓመት ጀምሮ  የከተማዋን  የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ የሚያዘምኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ስራ ላይ በማዋል የተቀናጀ የቆሻሻ አጠቃቀም ፕሮጀክት ተግባራዊ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ማስረሻው አስናቀ በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የከተማዋን የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ለማዘመን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተቀናጀ ቆሻሻ አወጋገድና አያያዝ ተግባራዊ ይደረጋል።

ለዚህም ከተያዘው ዓመት ጀምሮ ለሶስት ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ ፕሮጀክት የተቀረፀ መሆኑን  ጠቁመዋል።

ባዮ ጋዝ ማምረት፣ ኮምፖስትና  ኃይል ማመንጨት ፣ የሞተ እንስሳና የአደገኛ ደረቅ ቆሻሻ ማቃጠያ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ  እንደሆነ ነው የገለጹት።

ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ በዓለም ላይ ካሉ ቴክኖሎጂዎች የተሻለው እየተመረጠ መሆኑን አመልክተው፤ ይህም እንደተጠናቀቀ ቴክኖሎጂውን ለመግዛት ጨረታ እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

ደረቅ ቆሻሻን ወደ ሃብትነት ለመቀየር ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የተናገሩት።

ፕሮጀክቱን ለማስጀመር ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበ ሲሆን፤ ከዘንድሮው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም አቶ ማስረሻው አስታውቀዋል።

ኤጀንሲው ቀደም ሲል በነበሩት 72 የቆሻሻ ማንሻ ተሽከርካሪዎች ላይ የገጠመው አቅጣጫ መጠቆሚያ (ጂ ፒ ኤስ) አሁን ባሉት ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲሆኑ ለማድረግ ከመረጃ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር እየሰራ መሆኑንም ነው ምክትል ስራ አስኪያጁ ያመለከቱት።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ