አርዕስተ ዜና

በምስራቅ ወለጋ በ143 ሺህ ሔክታር ላይ የተፋሰስ ልማት ለማካሔድ ዝግጅት ተደርጓል

31 Dec 2017
479 times

ነቀምቴ ታህሳስ 22/2010 በምሥራቅ ወለጋ ዞን  በዘንድሮው የበጋ ወራት በ143 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ  የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ለማካሔድ ዝግጅት መደረጉን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና  አጠቃቀም  ቡድን መሪ አቶ ጌታሁን ተስፋዬ እንዳስታወቁት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራው የሚካሄደው በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎችና በ286 የገጠር ቀበሌዎች በተመረጡ 286 ንኡስ ተፋሰሶች ላይ ነው፡፡

143 ሺህ ሄክታር በሚሸፍነው በእነዚሁ ንኡስ ተፋሰሶች እርከን፣ የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮች፣ እርጥበትን የሚያቆዩ ስትራክቸሮችና የክትር ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡

እንዲሁም  44 ሺህ 119 ሄክታር የለማ መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ እንደሚከለል ተናግረዋል ።

በመጪው ጥር ወር አጋማሽ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀውን የተፋሰስ ልማት ስራ የሚመሩና የሚያስተባብሩ የዞንና የወረዳ የእርሻና  የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች፣ የልማት ጣቢያ ሠራተኞችና ተቆጣጣሪዎች ሥልጠና ወስደው እለቱን እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በልማት ስራው ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የዞኑ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ጌታሁን አስረድተዋል፡፡

የጉቶ ጊዳ ወረዳ  የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ባለሙያ አቶ መሐመድ አሰፋ በሰጡት አስተያየት ስራውን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ለአስፈፃሚ አካላት ስልጠና ተሰጥቷል ።

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ባለፉት አምስት ዓመታት በተካሄደው የተፋሰስ ልማት ስራ የመሬት ምርታማነት መጨመሩን፣ የደረቁ ምንጮች መጎልበታቸውንና የአካባቢው ሥነ ምህዳር እየተስተካከለ መምጣቱን ከአቶ ጌታሁን ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ