አርዕስተ ዜና

ከዘጠኝ ሺህ በላይ ተፋሰሶች የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል Featured

31 Dec 2017
518 times

ታህሳስ 22/2009 በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 9 ሺህ 506 ተፋሰሶችን በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ለመሸፈን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በሚኒስቴሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ባለሙያ ወይዘሪት ፈትለወርቅ በቀለ እንደገለፁት የተፈጥሮ ሃብት መመናመንና መራቆትን በመቀነስ  ምርታማነትን ለማሳደግ ዘንድሮ ከጥር 1 ጀምሮ በ829 አዲስና በ8ሺህ 677 ነባር የማህበረሰብ ተፋሰሶች ላይ የልማት ስራው ይከናወናል፡፡

በህዝብ ንቅናቄ ስራ አርሶ አደሮችን በ304 ሺህ 255 የልማት ቡድኖችና ከአንድ  ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ በ1ለ5 በማደራጀት ስራውን ውጤታማ ለማድረግ እንቅስቃሴ እንደሚደረግም ተገልጿል።

ለዚሁ ሥራ የሚያገለግሉ ከ10 ነጥብ4 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የእጅ መሳሪያዎችና ከአራት መቶ ሺህ በላይ የቅየሳ መሳሪያዎችም ጥቅም ላይ ይውላልም ብለዋል።

በዚህም ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የሃገር ውስጥና የውጭ ዝርያ ያላቸው የዛፍ ችግኞች ፣ ለእንስሳት መኖ እንዲሁም ጎርፍን ለመከላከል ጠቀሜታ ያላቸው የሳር ዝርያዎች ተከላ ይከናወናል፡፡

ወጣቶች፣ ሴቶችና መሬት አልባ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማደራጀት ያገገሙ ተፋሰሶችን አልምተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ 55ሺህ ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም ባለሙያዋ ገልፀዋል፡፡

እቅዱን ለማሳካት የሚያስችሉ ሥልጠናዎች ለተለያዩ የግብርና ባለሙያዎች፣ ለቀያሽ አርሶ አደሮች እንዲሁም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አመራሮች እየተሰጠ ነው፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃበት ጥበቃ ባለሙያ አቶ አቢሹ ወንበረ እንዳሉት በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የሚከናወነው በጥናት በተለዩ 339 ተፋሰሶች ላይ ነው።

በተፋሰሶቹ ለማከናወን ከታቀዱት መካከል የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን፣ የክትር፣ የውሃ መቀልበሻ ቦዮች፣ የቦረቦር መሬቶችን ከንክኪ መከላከልና የችግኝ ዝግጅት ሥራ ተጠቃሽ ናቸው ።

በክልሉ በስራው  ላይ ከ124 ሺህ በላይ ህዝብ ይሳተፋል ያሉት ባለሙያው ለስራው አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎችም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልም ሶስት ሺህ አዲስና ነባር ተፋሰሶች ተለይተው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናቸውን በክልሉ ግብርና ቢሮ የአፈርና ውሃ ልማትና ጥበቃ ባለሙያው አቶ ቦጋለ ሌንጫ አስታውቀዋል፡፡

በልማት ስራውም  እስካሁን 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተሳታፊ  አርሶ አደሮች የተለዩ ሲሆን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማቱን ለሚመሩ ባለሙያዎችና ቀያሽ አርሶ አደሮች ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

ለልማቱ ከስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ቀላል የእጅና የቅየሳ መሳሪያዎች ለስራ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ በሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ከ20 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉም ወይዘሪት ፈትለወርቅ አስታውቀዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ