አርዕስተ ዜና

የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራው የአርሶ አደሩን ሕይወት በሚቀይር መልኩ ሊሆን ይገባል---አቶ ገዱ አንዳርጋቸው Featured

31 Dec 2017
543 times

 ባህር ዳር ታህሳስ 21/2010 በአማራ ክልል የሚናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የአርሶ አደሩን ሕይወት በዘላቂነት በሚቀይርና ለወጣቱ የሥራ ዕድል በሚፈጥር መልኩ መከናወን እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አሳሰቡ።

 በክልሉ በመጭው ጥር ወር በግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናውን ዝግጅት ተደርጓል።

 ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ዛሬ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ንቅናቄ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ሲጀመር እንደገለጹት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ በህዝቡ ሙሉ ተሳትፎ ሲሰራ ቆይቷል።

 ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ከአካባቢ አካባቢ ልዩነት ቢኖረውም በየዓመቱ የጥራት ደረጃው እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

 "የተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የተሟላ ውጤት አመጣ ተብሎ ሊወሰድ የሚችለው ለአርሶ አደሩ የማይነጥፍና ቀጣይነት ያለው ገቢ የሚያስገኝ መሆን ሲችል ነው" ብለዋል።

 በመጭው ጥር ወር የሚጀመረው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራም የአፈር መከላትን ከመጠበቅና ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሊያመጣ በሚችል መልኩ ታስቦ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

 ቀደም ሲል የተለዩ ጉድለቶችን በማረም በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በሰብል፣ በመስኖና በደን ልማት፣ እንዲሁም ለወጣቶች የሥራ ዕድል በሚፈጥር መልኩ መከናወን አለበት ብለዋል።

 የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አይተነው እንደሻው በበኩላቸው እንዳሉት ያለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የአርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል ከባድ ነው።

 "የተሻለ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ በተሰራባቸው አካባቢዎችም ደርቀው የነበሩ ምንጮች ከመፍለቅ ባለፈ የወንዞች ፍሰት እየጨመረ በመምጣቱ አርሶአደሩ ከተፋሰሶቹ ተጠቃሚ እየሆነ መጥቷል" ብለዋል።

 በለሙ ተፋሰሶች 177 ሺህ 460 የሚሆኑ ወጣቶች በደንና ደን ውጤቶች፣ በንብ ማነብ፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፎች እንዲሰማሩ ተደርጓል።

 በያዝነው ዓመትም ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ለሚከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሰው ኃይል መለየቱን አረድተዋል።

 የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራው እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በህዝቡ ተሳትፎ ለመፈፀም የንቅናቄ መድረኮችን እስከ መንደር ድርስ በማከናወን በመጪው ጥር 7 ቀን 2010 በይፋ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

  ለሁለት ቀናት በሚቆየው ክልል አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ንቅናቄ መድረክ ላይ በምዕራብ አማራ ከሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም አጋር አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 በክልሉ ባለፉት ዓመታት ወደልማት በገቡ ከ18 ሺህ በላይ ተፋሰሶች በተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ለምነቱን አጥቶ የነበረ ከ 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መልሶ ማገገሙ ታውቋል ።  

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ