አርዕስተ ዜና

በትግራይ ደቡባዊ ዞን ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት ለደን ልማት እየተካለለ ነው

356 times

ማይጨው ሚያዝያ  3/2010 በትግራይ ደቡባዊ ዞን ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት ለደን ልማት ለማዋል የማካለል ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ አቻምየለህ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት የማካለሉ ሥራ 178 ተፋሰሶችን መሰረት አድርጎ እየተካሄደ ነው።

ለደን አገልግሎት እየተከለለ ያለው ቦታ ባለፉት ዓመታት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተካሄደበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማካለሉ ሥራ በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ መሆኑን የገለጹት አቶ አቻምየለህ፣ የደን ልማቱ የአካባቢው ማህበረሰብ ሀብት መሆኑን ለማረጋገጥ በቀበሌ ምክር ቤቶች የማፀደቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አቶ አቻምየለህ ገለጻ በሚከለለው የደን ሥፍራ በመጭው ክረምት የችግኝ ተከላ ሥራ ይከናወናል ብለዋል ።

"እየተከለለ ያለው ቦታ እርከን የተሰራለት በመሆኑ ከአፈር መሸርሸር አዳጋ የተጠበቀ ነው" ያሉት ደግሞ የራያ አላማጣ ወረዳ አርሶአደር አባዲ ሹመይ ናቸው።

የሚከለለው ስፍራ በተራራ ስር ላሉ እርሻዎች የአፈር ለምነትና እርጥበት ለመጠበቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አመላክተዋል ።

ከዚህ ቀደም በተከለሉ ሥፍራዎች ለእንስሳት ቀለብና ለቤት ክዳን የሚሆን ሳር በበቂ ሁኔታ እያገኙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የአምባላጌ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሽዋየ አብርሃ ናቸው።

" አሁን ላይ እየተከለለ ያው ስፍራም ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጠን በመሆኑ በባለቤትነት እንክበካቤ እናደርግለታለን " ብለዋል ።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን