አርዕስተ ዜና

በዞኖቹ ከ600 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚሳተፍበት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ይካሄዳል

25 Nov 2017
1505 times

ጎንደር ህዳር 16/2010 በሰሜን፣ በማዕከላዊና በምዕራባዊ ጎንደር ዞኖች በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ600 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚሳተፍበት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን ተገለጸ፡፡

በ2009 በጀት ዓመት በጋ ወራት በዘርፉ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ወረዳዎች፣ የግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች የእውቅና ምስክር ወረቀትን ጨምሮ የዋንጫና የኮምፒውተር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በጎንደር ከተማ በተዘጋጀው የተፈጥሮ ሀብት ፌስቲቫል ላይ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ እንደተናገሩት በዘንድሮ የበጋ ወራት በሦስቱ ዞኖች በጥናት የተለዩ 900 ነባርና 32 አዲስ ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ይከናወናል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ በዘንድሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የአርሶ አደሩን ጉልበት በአግባቡ በመጠቀም ቀጣይነትና ዘላቂነት ባለው መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡

በየደረጃው በተካሄደ ውይይት ሕብረተሰቡ በየአካባቢው በሚካሄድ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ ከ20 አስከ 30 ቀናት ለመሳተፍ የጋራ ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል፡፡

"የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራው በዞኖቹ ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ይጀመራል" ብለዋል ።

በ2009 ዓ.ም በዘርፉ ባከናወነው ሥራ የዋንጫና የኮምፒውተር ተሸላሚ የሆነው የጣቁሳ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ይርጋ ብዙአየሁ እንደገለጹት ሽልማቱ ሕብረተሰቡን ለበለጠ ውጤት ያነሳል።

በወረዳው የለሙ ተፋሰሶችን ከሰውና ከእንስሳ ንክኪ በመጠበቅና ሕብረተሰቡን ከተፋሰስ ልማቱ ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ውጤታማ ተግባር ማከናወኑን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የግብርና ስራዎች የዋንጫና የኮምፒውተር ተሸላሚ የሆነው የበየዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀናው አሰፋ በበኩላቸው፣ ወረዳው ርጥበት አጠር በመሆኑ የተፈጥሮ ሀብቱንና የሰብል ልማቱን በማቀናጀት ውጤት ማስመዘግብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሕብረተሰቡ ተሳትፎ 40 ተፋሰሶች ከሰውና ከእንስሳ ንክኪ ነጻ ሆነው ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ቀናው ገለጻ ሽልማቱ ለሕብረተሰቡ ተሳትፎ እውቅና የሰጠ ነው።

"የወረዳውን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ከደን ምንጣሮ፣ ቃጠሎና ከህገ ወጥ እርሻ ለመከላከል ከባልደረቦቼ ጋር በመሆን ላከናወንኩት ተግባር እውቅና በማግኘቴ ደስታ ተሰምቶኛል " ያሉት ደግሞ የታች አርማጭሆ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ዮሐንስ ምስጋናው ናቸው፡፡

በተካሄደው የሽልማትና የእውቅና አሰጣጥ ስነ ስርአት ላይ በ2009 ዓ.ም በተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ የበየዳ ወረዳ፤ በግብርና ሥራ ደግሞ የጣቁሳ ወረዳ የላቀ አፈጻጸም በማከናወን እያንዳንዳቸው የዋንጫና የኮምፒውተር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በተጨማሪም ግንባር ቀደምና ሞዴል ለሆኑ አርሶ አደሮች እንዲሁም የልማት ጣቢያ ሠራተኞችና ቡድን መሪዎች በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የቤት ውስጥ መብራትን ጨምሮ ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ በሽልማት መልክ መበርከቱን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡ 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ