አርዕስተ ዜና

በመጭዎቹ አስር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ አመቺ መሆኑ ተገለጸ Featured

23 Nov 2017
1568 times

አዲስ አበባ ህዳር 14/2010 በመጨረሻዎቹ አስር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ አመቺ መሆኑን ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ ከህዳር 10 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች የበጋው ደረቅ የአየር ሁኔታ አመዝኖ የሚቆይ በመሆኑ አርሶ አደሮች ይህንን አመቺ ሁኔታ ተጠቅመው ሰብላቸውን እንዲሰበስቡ መክሯል፡፡

የበጋ ወቅት እርጥበት ተጠቃሚ በሆኑ የምዕራብ፣የደቡብ ምዕራብ፣የደቡብና የደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች እርጥበቱ በስርጭትም ሆነ በመጠን የሚዳከም ቢሆንም የተገኘውን እርጥበት ጥቅም ላይ ማዋል እንዲቻል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግም አሳስቧል፡፡

ዝናብ በሚጠበቅባቸው በደቡብና በደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚኖረው ዝናብ አነስተኛ መጠን ያለው እንደሚሆን የሚጠበቅ ሲሆን፤የሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎችም ጥቂት ቦታዎች አነስተኛ ዝናብ የማግኘት እድል እንደሚኖራቸው ትንበያው ይጠቁማል፡፡

በጥቂት የደቡብ ኦሮሚያ፣ጋምቤላ፣ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እንዲሁም በደቡብ ሶማሌ፣በአርሲና ባሌ መደበኛ እና ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ ይጠበቃል፡፡

በምስራቅና በደቡብ ትግራይ እንዲሁም በጥቂት የምስራቅ አማራ አካባቢዎች አነስተኛ ዝናብ እንደሚኖር ተጠቁሟል፡፡

በቀሪዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ደረቅ፣ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ አመዝኖባቸው የሚቆይ ሲሆን በጥቂት የአገሪቱ ደጋማ አካባቢዎች የለሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ከሞላ ጎደል እንደሚቀጥልም ይጠበቃል፡፡

ገናሌ ዳዋ፣ባሮ አኮቦ፣የታችኛው ሪፍት ቫሊ፣አብዛኛው ኦሞ ጊቤ፣የታችኛው ኦጋዴን፣የላይኛው ዋቢሸበሌ እና የአዋሽ ተፋሰስ የውሃ ክፍሎችም ከመደበኛው በታች ዝናብ የሚያገኙ ሲሆን  ለግጦሽ ሳርና ለግድቦች የሚጠቅም ይሆናል፡፡

የታችኛው ተከዜና የላይኛው አባይ አካባቢዎች አነስተኛ ዝናብ እንደሚያገኙ የሚጠበቅ ሲሆን የተቀሩት ተፋሰሶች ደረቃማ የአየር ሁኔታ በሚያስተናግዱ አካባቢዎች ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ተጠቁሟል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ