አርዕስተ ዜና

የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ የማሳችንን የአፈር ለምነት በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ አስችሎናል - የሰከላ ወረዳ አርሶ አደሮች

552 times

ባህር ዳር መጋቢት 27/2010 በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ አርሶ አደሮች የሚያከናውኑት የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ የማሳቸውን የአፈር ለምነት በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ እንዳስቻላቸው ተናገሩ።

በወረዳው የኮለል ለቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ስሜነህ ሞላልኝ እንደገለጹት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ከመጀመሩ በፊት ጋራ የበዛበት አካባቢያቸው የአፈር ለምነቱ የተሟጠጠ ነበር። 

በተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የአካባቢው ልምላሜ በመመለሱ የማሳቸው አፈር ለምነት እንዲሻሻል አድርጓል፡፡

ጥቅሙን በመረዳታቸውም ባለፈው ጥር ወር በተጀመረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ያለማንም ቀስቃሽ መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለአንድ ወር ያካሄዱትን የልማት ስራ አጠናቀው ለቀጣዩ የመኽር ልማት የእርሻ ስራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በወረዳው የአባይ ሳንግብ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወንድም ተሻለ በበኩላቸው በየዓመቱ የሚሰሩት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች የማሳቸው አፈር ለምነት መጨመር የሰብል ምርት መጠኑን እንዳሳደገላቸው ነው ያነሱት።

ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በ551 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ባለሙያ አቶ ፈጠነ መኮንን ተናግረዋል።

ስራው የተከናወባቸው 2 ሺህ 192 ተፋሰሶችም የአፈር ክለትን ከ77 ቶን ወደ 34 ቶን ዝቅ እንዲልና የውሃ ፍሰቱ እንዲጨምር ማስቻሉ በጥናት መረጋገጡን ጠቁመዋል።

ይህም የአፈር ለምነቱ እየተሻሻለ በመምጣቱ በሄክታር በአማካኝ ዘጠኝ ኩንታል የምርት ጭማሪ እንዲኖር ማድረጉን አስረድተዋል።

በዘንድሮው የበጋ ወራትም ከግማሽ ሚሊየን የሚበልጡ የዞኑ አርሶ አደሮች 40 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን ስራዎች መከናወናቸውንም አስታውቀዋል። 

4 ሺህ 452 ሄክታር የተራቆተ መሬትን በመከለል ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ እንዲጠበቅ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።  

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን