አርዕስተ ዜና

በጣንቋ አበርገለ ወረዳ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ያገኙትን መልካም ውጤት እንደሚያስቀጥሉ አርሶ አደሮች ተናገሩ

21 Nov 2017
1578 times

አክሱም ህዳር 12/2010 የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራን በማጠናከር ያገኙትን  መልካም ውጤት እንደሚያስቀጥሉ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ጣንቋ አበርገለ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡ  አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

የትግራይ ህዝብ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርሃማነት በመከላከልና  አረንጓዴ ልማትን በማካሄድ ባስመዘገበው የተሻለ ውጤት የተበረከተለት  የወርቅ ሽልማት ወደ ወረዳው ሲገባ የአካባቢው አርሶ አደሮች አቀባበል አድርገውለታል፡፡ 

ከወረዳው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ማሞይ ጸጋይ ለኢዜአ እንዳሉት ፣ ሽልማቱ የትግራይ አርሶ አደር በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ  ስራ ለብዙ ዓመታት ሳይታክት ላከናወነው ጥረት የተሰጠ እውቅና ነው።

የሚኖሩበት ወረዳ ቆላማና ተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃው እንደነበር ያመለከቱት አርሶ አደሩ፣ "ባከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አሁን ድርቅን የሚቋቋም አረንጓዴ አካባቢ እየተፈጠረ መጥቷዋል "ብለዋል።

በዚህም ለግብርና ስራቸው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመው  ወጣቱ በንብ ማነብና በእንስሳት ማድለብ ስራ ተሰማርቶ ተጠቃሚ መሆን መጀመሩን ገልጸዋል።

" የተሰጠን አለም አቀፍ የእውቅና ሽልማት የተጀመረውን የአረንጓዴ አካባቢ ልማት ለማፋጠን አቅምና ብረታት ይሆነናል፣በዘርፉ የበለጠ እንድንሰራ ያነሳሳናል " ብለዋል አርሶ አደርአቶ ማሞይ ።

አርሶ አደር ዲያቆን ጸጋይ ተጫነ በበኩላቸው፣ ሽልማቱ ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ አጠናክሮ በማስቀጠል  የተገኘውን መልካም ውጤት  በመስኖ ልማትና በሌሎች የግብርና ስራቸው ላይ  ለመድገም እንደሚያነሳሳቸው ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ በነጻ የጉልበት ተሳትፎውና ጥረት  በአፈርና ውሃ ጥበቃ ተከታታይ ስራ  በማከናወኑ ተጎድቶ የነበረው የተፈጥሮ ሃብት ወደ ነበረበት የቀድሞ ሁኔታው እየተመለሰ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በጥረታቸው ባስመዘገቡት ውጤት ያገኙት እውቅና እንደሚገባቸው የተናገሩት ደግሞ  የወረዳው ሴት አርሶ አደር  ወይዘሮ ዘምዘም በርሄ ናቸው።

በሌሎች ዘርፎችም መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣትና የተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ሰራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደጀን በርሄ እንዳሉት፣ አለም አቀፍ እውቅናውና ሽልማቱ የመላው የትግራይ ህዝብና በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አመራር አካላት የጋራ ጥረት ነው።

ሽልማቱ ኢትዮጰያ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የምትከተለው ፖሊሲና የስራ ውጤት  መሆኑንም ጠቅሰዋል።

" በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድረን ለሽልማት መብቃታችን ታላቅ ደስታና ስሜት የሚፈጥር ነው "ያሉት  አቶ ደጀን፣ ሽልማቱ ወደ ተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች ሲዘዋወር የቀሩን ሰራዎች ለሟሟላት አርሶ አደሩን ለማነሳሳት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ በተገኘው ሽልማትና ውጤት ሳይዘናጋ የጀመረውን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ ስራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

የትግራይ ክልል በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ባስመዘገበው ውጤት የተሸለመው ወርቅ በቅርቡ ቻይና አገር ኦርደስ ከተማ  በተከናወነው  ስነስርዓት ርዕስ መስተዳድር አባይ ወልዱ መረከባቸውን በወቅቱ ተገልጿል፡፡

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ