አርዕስተ ዜና

በሶማሌ ክልል የሚገኘውን 'ይዒብ' የቆላ ዛፍ ከተጋረጠበት የመጥፋት አደጋ ለመከላከል እየተሰራ ነው

20 Nov 2017
1454 times

ጂግጀጋ ህዳር 11/2010 በሶማሌ ክልል የሚገኘውን 'ይዒብ' የቆላ ዛፍ ከተጋረጠበት የመጥፋት አደጋ ለመታደግ የሚያስችል ማህበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የግብርና ኮሌጅ ዲን እና የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዶክተር ሙሴ መሐመድ ለኢዜአ እንዳሉት በአካባቢው ማህበረሰብ "ይዒብ" እንዲሁም በሳይንሳዊ አጠራር "ኮንዳዥያ ኢዱሊስ" በሚል ስያሜ የሚታወቀው ዛፍ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል።

በሶማሌ ክልል ዋርዴር ወረዳ ዛፉ ከሚገኘባቸው ቀበሌዎች መካከል ገንበዴ አንዱ መሆኑን ገልጸው በቀበሌው የሚኖሩ ከፊል አርብቶ አደሮች የድርቅ አደጋን ለመቋቋም እንዲችሉ ዛፉን በማሳቸው እንዲያለሙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለከፊል አርብቶ አደሮቹ በችግኝ አተካከልና እንክብካቤ ላይ ቴክኒካል ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ድርቅ ለመቋቋም ይዒብ የቆላ ዛፍ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው መሆኑን ጠቁመው፣ ዛፉ የውሃ እጥረትን ተቋቁሞ በማንኛውም ወቅት ፍሬ እንደሚሰጥና ለሰውና ለእንስሳት ምግብነት እንደሚውል አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያና አጎራባች ሱማሊያ ድንበር አካባቢ በስፋት ይገኘ የነበረው ይዒብ ዛፍ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በኩል ያለው ብቻ ፍሬ እየሰጠ ነው።

ይሁንና ዛፉ  ለማገዶና ለቤት መስሪያ በስፋት የመጠቀሙሁኔታ በመኖሩና ዛፉን በባለቤትነት የሚንከባከብ አካል ባለመኖሩ ለመጥፋት አደጋ መጋለጡን አስረድተዋል።

ዛፉን ከመጥፋት አደጋ ለመታደግ  አንድ ሺህ ችግኞች በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የማልማት ሥራ በከፊል አርብቶ አደሮች መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ከፊል አርብቶ አደሮች የተከሉት የይዒብ ዛፍ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ፍሬ የሚሰጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።

"ተክሉ የአርብቶ አደሩን እና የቤት እንስሳቱን የድርቅ ተጋላጭነት በመቀነስ ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ ፍሬው በገበያ ተፈላጊነት ያለው በመሆኑ በኪሎ ግራም 120 ብር የሚሸጥ በመሆኑ አመራጭ የገቢ ምንጭ ይሆናል" ብለዋል፡፡

የሶማሌ ክልል እንስሳት እርባታና ከፊል እርሻ ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ ጉሌድ አው አሊ " ይኢብ ለሶማሌ ክልል ከፊል አርብቶ አደር ነዋሪዎች የተፈጥሮ ስጦታ የሆነ ወሳኝ ተክል ነው" ብለዋል ፡፡

የክልሉ መንግስት፣ በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር አካላትና ማህበረሰቡ ዛፉ እንዳይጠፋና በምንም መልኩ በህገ ወጥ መንገድ እንዳይቆረጥ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

"ይዒብ ዛፍ ከአምስት ዓመታት በፊት በክልሉ አምስት ወረዳዎች በስፋት ነበረ" ያሉት አቶ ጉሌድ በአሁኑ ወቅት ዝርያው ተመናምኖ በሁለት ቀበሌዎች ብቻ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በሶማሌ ክልል ዋርዴር ወረዳ ገምቤሬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መሀመድ አህመድ በበኩላቸው ዛፉ ባአካባቢያቸው እየተስፋፋ እንዲመጣ ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በክልሉ ድርቅ ተከስቶ በነበረብት ወቅት ብዙ ሰዎች ከጎረቤት ሀገር ሱማሊያ ጋልካሀዮ አካባቢ መጥተው ተክሉን ለእንስሳቶቻቸው ከማብላት ባለፈ ዛፉን ቆርጠው ለቤት ውስጥ ፍጆታ ማዋላቸው እንዲመናመን እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል። 

ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ከሶማሌ ክልል እንስሳት እርባታና ከፊል እርሻ ምርምር ተቋም ጋር በመቀናጀት ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት የሚቆዩ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ስራዎች እያከናወነ ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ