አርዕስተ ዜና

በሶማሌ ክልል እየጣለ ያለው የበጋ ወቅት ዝናብ ለእንስሳት ግጦሽና ለመጠጥ ውሃ አመቺ መሆኑ ተገለጸ

13 Nov 2017
1455 times

ጂግጀጋ ህዳር 4/2010 በሶማሌ ክልል እየጣለ ያለው የበጋ ወቅት  ዝናብ  ለእንስሳት ግጦሽና ለመጠጥ ውሃ  አቅርቦት አመቺ  መሆኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ የሜትሮሎጂ ኤጀንሲ የጅግጅጋ ቅርንጫፍ አስታወቀ፡፡

በክልሉ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ በመደበኛ ሁኔታ የሚዘልቀው የበጋ ወቅት ዝናብ በአካባቢው  "  ዳይር "   በሚል መጠሪያ ይታወቃል፡፡

የቅርንጫፉ የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ አቶ በላይነህ አያል ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በአብዛኞቹ  ዞኖች  ቀጥሎ ያለውዝናብ ካለፈው ዓመት የተሻለ ስርጭት አለው፡፡

የ" ዳይር"  ዝናብ ተጠቃሚ አርብቶ አደር አካባቢዎች በሆኑ ደጋህቡር ፣ቆራሃይ፣ ሸበሌ፣አፍዴር ሊባን፣ ዳዋ፣ ዶሎ፣ ኤረርና ኖጎብ እየጣለ ይገኛል፡፡

የዝናቡ  ስርጭት ለእንስሳት የግጦሽ ሳር፣ ለቁጥቋጦ ልምላሜ እና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

የዝናቡ አዝማሚያ  ከሁለት ሳምንት በኋላ አወጣጡ እየቀነሰ እንደሚሄድ ባለሙያው  የትንበያ መረጃዎችን ጠቅሰው  አመልክተዋል፡፡

በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የእርሻ ልማት ማስፋፊያና ኤክስቴንሽን ስራ ሂደት መሪ አቶ አህመድኑር መሀድ በበኩላቸው  እያጣለ ያለው ዝናብ ከፋፈንና ሲቲ ዞኖች በስተቀር በክልሉ ዋና የዝናብ ወቅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም   ከፊል አርብቶ አደሮች ማሽላና በቆሎ ሰብል ማልማት ጀምረዋል፡፡

በጀረር፣ በአፍዴር፣በቆራሃይ፣ በኖጎብ፣ በሊባንና በሸበሌ ዞኖች የሚገኙ ከፊል አርብቶ አደሮች የወቅቱን የዝናብ ውሃ በመጠቀም ከሚያደርጉት የሰብል ልማት በተጓዳኝ  በልማት ቡድኖችና  በቤተሰብ ደረጃ በመቀናጀት የዝናብ ውሃን በባህላዊ መንገድ በማሰባሰብ ላይ እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡  

እየጣለ ያለው ዝናብ  በድርቁ ምክንያት  የነበረውን   የሰውና የእንስሳት የመጠጥ ውሃ ችግር እንደሚያቃልል የገለጹት ደግሞ በክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ስራ ሂደት መሪ አቶ አብዲ አህመድ ናቸው፡፡

በዶሎ ዞን ዋርዴር ወረዳ የገርሎጎባይ ቀበሌ አርብቶ አደር አቶ መሐመድ መሀሙድ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተከታታይ ቀናት የጣለው ዝናብ በድርቁ ምክንያት ተጎድተው የነበሩ የተለያዩ የቤት እንስሳት  የግጦሽ ሳር ማግኘት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀበሌው በክልሉ መንግስት የተገነባው የዝናብ ውሃ ማሰባሰቢያ ግድብ በቂ ውሃ ማጠራቀሙን ጠቁመው  በዚህም ለራሳቸውም ሆነ ለቤት እንስሳት  ውሃ  ማግኘት እንደቻሉም ጠቅሰዋል፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ