አርዕስተ ዜና

ኢትዮጵያ በጉባዔው የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ድርድሮች ለማድረግ ተዘጋጅታለች

03 Nov 2017
1775 times

አዲስ አበባ ጥቅምት24/2010 ኢትዮጵያ በመጪው ሰኞ በሚጀመረው የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ድርድሮች ለማድረግ መዘጋጀቷን ገለጸች።

 የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሩ ዶክተር ገመዶ ዳሌ ዛሬ በሰጡት መግለጫ "ኢትዮጵያ በጉባኤው ለመሳተፍ ዝግጅቷን ከወዲሁ አጠናቃለች" ብለዋል።

 ኢትዮጵያ በአነስተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ አገራት መሪ በመሆኗ የአገራቱን አቋምና ፍላጎት የሚያንጸባርቁ 20 ሰነዶች አዘጋጅታ ለጉባኤው ልካለች።

 ከዚህ ቀደም እንደ አገር በዘርፉ ሲደረጉ የቆዩ ተግባራትና መልካም ተሞክሮዎችን በጉባኤው በተሳካ መልኩ ማቅረብ የሚያስችል ቡድንም ተዘጋጅቷል።

 በዚሁ መሰረት ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የተውጣጡ 24 ተወካዮችና ከሙያ ማኅበራት የተውጣጡ 30 ግለሰቦች መመልመላቸውን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

 የልዑካን ቡድኑ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን ስትራቴጂ በተመለከተ ሥልጠና እንደተሰጣቸውና ይህም በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያን አቋም በስፋት ለማንጸባረቅ እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።

 ጎን ለጎንም ቡድኑ በጉባኤው ላይ የአገሪቱን የአየር ንብረት ለውጥ የፖሊሲ አቅጣጫና ስትራቴጂ ለሌሎች አገራት ቡድኖች ለማካፈል ይሠራል ነው ያሉት።

 ቡድኑ በተጓዳኝ ስልቱን ሊደግፉ ከሚችሉ አገራትና ድርጅቶች ጋር የሁለትዮሽ የጋራ ትብብር ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀስ አብራርተዋል።

 የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ድርድር በማድረግ አገሪቱ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ያላትን የዲፕሎማሲ መሪነት ድርሻ ለማስቀጠል ትሰራለች ብለዋል። 

 በሌላ በኩል በጉባኤው ላይ በፓሪሱ ስምምነት ላይ ዳግም ድርድር እንዳይቀርብ ኢትዮጵያ ከምትመራው 48 ታዳጊ አገራት ጋር ሆና ድምጿን እንደምታሰማ ገልጸዋል።

 ከፓሪስ ስምምነት በፊት ተግባራዊ እየተደረገ የነበረውን የማጣጣሚያ የገንዘብ ቋት ለፓሪሱ ስምምነት እንዲያገለግል ኢትዮጵያ ድጋፏን እንደምትሰጥም ተናግረዋል። 

 በፓሪሱ ሥምምነት አተገባበርን በተመለከተ ግልጸኝነት እንዲፈጠር በመደራደር በኩልም ኢትዮጵያ በአዎንታዊ መልኩ ተሳትፎ እንደምታደርግ ጠቁመዋል።

 24ኛው የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ በጀርመኗ ቦን ከተማ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ለአስር ቀናት ይካሄዳል።

 ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በሞሮኮ ማራከች ከተማ በተካሄደው የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ የታዳጊ አገሮች ድርድር መሪ ሆና መመረጧ ይታወቃል።

 በዚህም 48 ታዳጊ አገራትን በመምራት የአገራቱን አቋምና ፍላጎት በማንጸባረቅ በዘርፉ የበኩሏን እያበረከተች ትገኛለች።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ