አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በበጋ ወቅት የሚኖረው እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ለማሳ ዝግጅትና ለዘር አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተገለጸ Featured

02 Nov 2017
1827 times

አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2010 የደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ቆላማ የአገሪቱ ክፍሎች የሚያገኙት ዝናብ ለማሳ ዝግጅትና ዘር አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥርላቸው ብሔራዊ ሚቲዩሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ዛሬ የበጋ ወቅት የአየር ጠባይ አዝማሚያን አስመልክቶ ለኢዜአ እንዳስታወቀው የደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ቆላማ የአገሪቱ ክፍሎች በተያዘው ወር የሚጠበቀው እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ወቅታዊ ዝናብ ለሚያገኙት የአገሪቱ ክፍሎች የማሳ ዝግጅት ለማድረግና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

በአካባቢው ለሚኖሩት አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥሩ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ግምት ተጥሎበታል።

ከያዝነው ወር በኋላ ሊኖር የሚችለው ከመደበኛው ያነሰ ዝናብ በወቅቱ የግብርና ሥራ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ቢኖረውም የሚገኘውን ዕርጥበት ለበጋ የግብርና ስራዎች መቆጠብና መጠቀም ተገቢ መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል።

በተመሳሳይ ሁኔታም በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር መጠበቁ ቀደም ብለው ለተዘሩ፣ ፍሬ በመሙላት ላይ ለሚገኙ፣ ዘግይተው ለተዘሩና በተለያየ እድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የመኸር ሰብሎችም ሆነ ቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎትን ለሟሟላት ይረዳል።

በተጨማሪም በአርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለግጦሽ ሳር ልምላሜ የጎላ አስተዋኦ ይኖረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በአብዛኛው የሰሜን አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ ፀሐያማ እና ነፋሻማ የአየር ፀባይ ጎልቶ ሊታይ እንደሚችል ተጠቁሟል።

በተለይም በበጋው ወቅት ሰብል በደረሰባቸው አካባቢዎች ለሰብል ስብሰባና ድሕረ ሰብል ስብሰባው አመቺ ሁኔታን የሚፈጥር ቢሆንም በሌሊቱና በማለዳው ወቅት ቅዝቃዜ እንደሚስተዋል ይጠበቃል።

ይሕም በመደበኛ ሁኔታ በበጋ ወቅት በሚከሰተው ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ሳቢያ የሚፈጠር ውርጭ በአንዳንድ የመካከለኛው፣የሰሜንና የደቡብ ደጋማ የአገሪቱ ሥፍራዎች በሰብሎች እድገትና በእንስሳት ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ተገቢው ክትትል መደረግ ይኖርበታል ብሏል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ