አርዕስተ ዜና

ባለሀብቶችን በደን ልማት እንዲሰማሩ የሚያበረታታ የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ እየተዘጋጀ ነው

01 Nov 2017
1838 times

አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2010 ባለሀብቶችን በደን ልማት ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚያበረታታ የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ እየተዘጋጀ ነው።

 የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ያዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

 አዋጁ በቀድሞ መጠሪያው 'የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር' በ1999 ዓ.ም የተዘጋጀውን የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 542/1999 የሚያሻሽል ነው።

 የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የደን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ይማም እንዳሉት አዲሱ አዋጅ የተዘጋጀው በደን መጨፍጨፍና መራቆት ምክንያት ከፍተኛ አካባቢያዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተከሰቱ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ነው።

 አዋጁ ሲተገበር የደን ሽፋንን በማሳደግ የአየር ንብረትን መጠበቅ እንዲሁም የደን ውጤቶችን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ የደን ውጤቶችን ማስቀረት ያስችላል ብለዋል።

 አዋጁ ደንን የግል፣የማህበረሰብ፣የማህበራት፣የመንግስት ብሎ የሚመድባቸው ሲሆን ማህበረሰቡ ከመንግስት ደን በመትከል፣በመንከባከብ እና በጥበቃ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ ነው።

 በአዲሱ አዋጅ መሰረት ባለሀብቶችና ግለሰቦች በደን ልማት ዘርፍ እንዲሰማሩ ማበረታቻዎች የሚኖሩ ሲሆን የደን ሽፋኑ ሲያድግም ከካርቦን ሽያጭ ገቢ ማግኘት ያስችላል።

 አገር በቀል ዛፎች እየተመናመኑ ስለሆነ ማንኛውንም ደን መቁረጥ የሚከለክል እንዲሁም ማንኛውንም ያለ አግባብ በሚጨፈጭፉት ላይ ቅጣት የሚያስከትሉ አንቀጾችን አካቷል።

 የደን ውጤቶች ለሚመረትባቸው አካባቢዎችም የደን ውጤቶች አምራቹ የባለቤትነት ክፍያ እንዲከፍል የሚያስገድድ ነው።

 ህገወጥ የደን ጭፍጨፋንና የደን ውጤቶች ዝውውርን ለመከላከልም ከአርሶ አደሮች በስተቀር ድርጅቶችና ባለሀብቶች ምርቶችን ለመሸጥና ለማዘዋወር ፍቃድ ማግኘት ሲጠበቅባቸው በከተሞች መግቢያና መውጫ የደን ዝውውር መጠበቂያ ጣቢያዎችም ይከፈታሉ።

 ቋሚ ኮሚቴው በአዋጁ ያልተካተቱ ነገር ግን በሌሎች አዋጆች የተገለፁ ጉዳዮች በዚህ አዋጅ የሚካተቱና የሚሰሩ መሆኑ እንዲጠቀስና ሌሎች ማሻሸያዎችን በማድረግ በአንድ ሳምንት ውስጥ ድጋሚ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲቀርብ አሳስበዋል።

 አዋጁ በፀደቀ በሶስት ወራት ውስጥ ደንብና መመሪያዎች በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቀው ለማህበረሰቡ ደርሰው መተግበር ስላለባቸው  ጎን ለጎን እንዲዘጋጁም አሳስቧል

 የተሰጡ አስተያየቶች ተካተው  ሲመጡ ለውሳኔ ሀሳብ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ተገልጿል።

 በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ 58 የመንግስት ጥብቅ ደኖች እንዳሉ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ