አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የአምቦጭ አረምን ለማስወገድ የሚደርገውን ጥረት ለመደገፍ የሚያስችል የጣና ሃይቅና አካባቢ ደህንነት ፈንድ ተቋቋመ Featured

31 Oct 2017
1779 times

 ባህር ዳር ጥቅምት 21/2010  በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የአምቦጭ አርምን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት በተደራጀ መንገድ ለመደገፍ የሚያስችል የጣና ሃይቅና አካባቢ ደህንነት ፈንድ መቋቋሙን የክልሉ አካባቢ፣ ደን፣ ዱር እንስሳትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

 በመጤ አረሙ ከተወረረው የሃይቁ ክፍል አንድ ሺህ 400 ሄክታር በህብረተሰቡ ተሳትፎ ማስወገድ ተችሏል።

 የእምቦጭ አረምን የማስወገዱ ተግባር በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሊሆን አንደሚገባው ከካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የመጡ የስነ ህይዎት ተመራማሪ ገልፀዋል።

 የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የእምቦጭ አረሙን በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለማስወገድ ባለፉት ስድስት ዓመታት ሰፊ ርብርብ ሲካሄድ ቆይቷል።

 ይሁን እንጂ ከመጤ አረሙ አስቸጋሪ የመራባት ባህሪ የተነሳ እስካሁን የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም።

 አሁን ግን የህብረተቡን ያልተቆጠበ የጉልበት አስተዋጽኦ በገንዘብና በቴክኖሎጂ በማገዝ አረሙን በዘላቂነት ለማስገድ የሚያስችል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፈንድ መቋቋሙን ተናግረዋል።

 የተቋቋመው ፈንድ በዋናነት በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ገንዘብ በማሰባሰብ አረሙን ለማስወገድና የሃይቁን ዙሪያ ደህንነት በሚያስጠብቁ ስራዎች እንዲውል ይደረጋል ብለዋል።

 በአሁኑ ወቅትም የፌዴራልና የክልሉ መንግስት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ አራት የእንቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽኖችን ለመግዛት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 ለሌሎች ሦስት ባለሃብቶችም ማሽኑን ገዝተው ለማቅረብ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ገልፀዋል።

 የጎንደር ዩኒቨርስቲ ያሰራው ማሽን ሙሉ በሙሉ መጠናቀቀና በዚህ ሳምንት የሙከራ ስራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡

 ''የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በ19 ሚሊዮን ብር እያስራቸው የሚገኙት አራት ማሽኖችም በቀጣይ አራት ወራት ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል'' ብለዋል።

 በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለሚከናወኑ ስራዎች ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ዶክተር በላይነህ አብራርተዋል።

 በአሁኑ ወቅት አምስት ሺህ 396 ሄክታር መሬት በአረሙ የተወረረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ  ባለፈው ወር በተጀመረው ዘመቻ  ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን በማሳተፍ አንድ ሺህ 400 ሄክታሩን ማስወገድ ተችሏል።

 አሁን የተጀመረው የህብረተሰቡ ርብርብ ተጠናክሮ ከቀጠለም እምቦጭ የጣና ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ እንደሚቻልም አብራርተዋል።

 የዓለም አቀፍ የጣና ሃይቅ የመልሶ ግንባታ ህብረት ዳይሬክተርና  በካሊፎርኒያ የስነ ህይዎት ተመራማሪ ዶክተር ሰለሞን ክብረት በበኩላቸው የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ የሰው ሃይል፣ ማሽን መጠቀምና ስነ ህይዎታዊ ዘዴ መጠቀም ተመራጭ ዘዴዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

 በቀጣይ አምስት ዓመታት ለሚከናወነው የአረም ማስወገድ ስራዎች በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር የገንዘብ፣ የቴክኒክና የማቴሪያል ድጋፍ ለማድረግ ማህበሩ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

 በአሁኑ ወቅት በህብረተሰቡ እየተከናወ  ያለውን የእንቦጭ ማስወገድ ስራ በእውቀት ያልተደገፈ በመሆኑ መልሶ የመራባት እድሉ ሰፊ መሆኑን ገልፀዋል።

 ''የእንቦጭ አረም ሲወገድ በጎርፍም ሆነ በነፋስ መልሶ እንዳይሰራጭ ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ተቆፍሮ በመቅበር መልሶ ለአፈር ማደበሪያነትና ለእንስሳት መኖ የሚውልበት መንገድ መመቻቸት አለበት'' ብለዋል።

 ማህበሩም የእንቦጭ አረም ያለበትን ሁኔታ ከቦታው ድረስ በመሄድ የስርጭት መጠኑን በጥናት ያረጋገጠ ሲሆን ለዚህ የሚሆንም የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ሰነድ ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

 የጣና ሃይቅ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ህዝቦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ በዚሁ ጊዜ ተገልጿል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ