አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በትግራይ በ24 ሚሊዮን ብር የተገነባ የደን ዘር ማዕከል ለአገልግሎት ተዘጋጀ

29 Oct 2017
1857 times

መቀሌ ጥቅምት 19/2010 በትግራይ እየተካሄደ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል በ24 ሚሊዮን ብር ወጪ የደን ዘር ማዕከል ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎ ተዘጋጀ።

በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ክፍሎም አባዲ ትናንት ለኢዜአ እንደገለፁት ለማዕከሉ ግንባታ የዋለው ገንዘብ ከክልሉና ከጃፓን መንግስት በድጋፍ የተገኘ ነው።

ማዕከሉ ከመቀሌ ከተማ አቅራቢያ ወጣ ብሎ የተገነባ መሆኑን አመልክተዋል።

ማዕከሉ የሚሰበሰቡት የደን ዝርያ ዓይነቶችን  ለረዥም ጊዜ ለማቆየት ፣ የቆይታ ጊዜና ተስማሚነታቸውን ለመለየት የሚያስችል ዘመናዊ ቤተ- ሙከራና ማቀዝቀዣ አለው።

የደን ዘርን አጥቦና አድርቆ ለችግኝ ተከላ ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች የተሟሉለት እንደሆነም  አቶ ክፍሎም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በተለይ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን ኩታ ገጠም የደን ልማት ስራ ተስማሚ ዝርያዎችን ለይቶ በማቅረብ የደን  ልማትና ጥበቃ ስራውን ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንዳለው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

"ማዕከሉ ወደ ፊት ለደን ልማት የሚሆን ዘር በመሰብሰብ ለተሰማሩ ነጋዴዎች የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠት ይጀምራል " ብለዋል ።

ለመጥፋት የተቃረቡ የደን ዝሪያዎች ተሰብስበው የጥራት ደረጃቸውን በማሻሻል ለተጠቃሚ ለማቅረብ የሚያስችል የዘር ባንክ አገልግሎት  እንደሚሰጥ አመላክተዋል ።

ማዕከሉ በአንድ ጊዜ መቶ ኩንታል የደን ዘር ተቀብሎ የማቆየት አቅም አለው።

ከዚህ ቀደም ዘር በአርሶ አደሮችና በነጋዴዎች እየተለቀመ ወደ ችግኝ ማፍያ ማዕከላት እንደሚላክ  ያስታወሱት አቶ ክፍሎም በተለያዩ መንገዶች የሚሰበሰበው ዘር ጥራቱ ስለማይታወቅ የመብቀል እድሉ የተፈለገውን ያህል እንዳልነበረ ተናግረዋል ።

የማዕከሉ መገንባት ችግሩን እንደሚፈታና በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር  አቶ ክፍሎም አስታውቀዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ