አርዕስተ ዜና

የአለም አረንጓዴ ልማት ሳምንት በአዲስ አበባ ይከበራል Featured

09 Oct 2017
1191 times

አዲስ አበባ መስከረም 29/2010 የአለም አረንጓዴ ልማት ሳምንት በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ ይከበራል።

የ2017 የአለም አረንጓዴ ልማት ሳምንት "የአፍሪካ አረንጓዴ ልማትን ማሳደግ" በሚል መሪ ሐሳብ  ከጥቅምት 7-10/2010ዓ.ም ቀን በአዲስ አበባ እንደሚከበር ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

በዓሉ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር የሚዘጋጅ ሲሆን በጉባኤው  ከ300 በላይ የተለያዩ አገራት የሃይል ልማትና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች፣ በሃይል ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችና ውሳኔ ሰጭዎች ይሳተፋበታል ተብሏል።

በመድረኩም አገራት ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ያከናወኗቸው ተግባራት ይገመገማሉ፣የአረንጓዴ ልማትን በአፍሪካና በአለም ለማስፋፋት የመፍትሄ ሀሳቦችና የተለያዩ ጥናቶች ይቀርቡበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ለፓሪሱ ስምምነት ተግባራዊነት አገራት ሊያደርጉት ስለሚገባው አስተዋፅኦ እና የመንግስታቱ ድርጅት የዘላቂ የልማት ግቦች ስለሚሻሻሉበት ሁኔታም ይወያያሉ።

ውይይቱ ተሳታፊዎች ፋይናንስ ለሚያስፈልጋቸው የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ምንጮችን የሚያፈላለጉበት፣የታዳሽ ሀይል ኢንቨስትመንትን የሚያሳድጉበትም ይሆናል።

በማደግ ላይ ያሉ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚሰሩት ስራ የፋይናንስ ድጋፍ ማሳደግ፣የውሃና ምግብ እጥረትን ለመከላከል የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችሉ አማራጮች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአካባቢ ጥበቃ ላይ ዘላቂነት ያለው እና ከባቢያዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን መሰረት ያደረጉ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲዎችን ማሻሻልና መተግበር ውይይት የሚደረግባቸው ሌሎች አጀንዳዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 15 ዓመታት ለመተግበር የቀረጸቻቸውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂዎች ፋይዳ በመድረኩ ገለጻ በማድረግ ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ እንድታገኝና እስካሁን በዘርፉ ያከናወነቻቸውን ስራዎች ለዓለም ለማስተዋወቅ ይጠቅማታል ተብሏል።

በተጨማሪም በአገሪቱ እየተሰሩ ያሉና በአገልግሎት ላይ ያሉ የታዳሽ ሀይል ልማትና የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶችም በጉባኤው ተሳታፊዎች እንደሚጎበኙ ታውቋል።

ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት መቀመጫውን ደቡብ ኮሪያ ሲኡል በማድረግ አገራት ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ የዕውቀት፣የገንዘብና መሰል ድጋፎችን የሚያደርግ በመንግስታቱ ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማስፈጸም የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው። 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ