አርዕስተ ዜና

በትግራይ በዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው

09 Oct 2017
1783 times

መቀሌ መስከረም 29/2010 በትግራይ ክልል በዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮጀክት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች አካባቢን በመጠበቅና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል አበረታች ውጤት መገኘቱ ተገለፀ ።    

ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከእስያ ሃገራትና ከአለም ባንክ  የተውጣጡ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት ዳይሬክተሮችና ከፍተኛ የልዑካን ቡድን አባላት በትግራይ ክልል እንደርታ ወረዳ "ድድባ" ቀበሌ በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተገኙ ውጤቶችን ጎብኝተዋል።

በዚህም በፕሮጀክቱ ድጋፍና በህዝብ ትብብር በወረዳው ባሉ አምስት ቀበሌዎች ውስጥ በ12 ተፋሰሶች ላይ በተከናወኑ የእርከን፣ ክትርና ሌሎች የአፈረና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ያገገሙ አካባቢዎችን ተመልክተዋል።

የልዑካን ቡድን አባላቱ በዚህ ወቅቱ እንዳሉት፣ ህዝቡ ባከናወናቸው የአረንጋዴ ልማትና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች አካባቢውን ከአፈር መከላት አደጋ መታደግ እንደተቻለ ግንዛቤ አግኝተዋል።

የ"ግሎባል ኢንቫይሮመንት ፋሲሊቲ" ተወካይ ዶክተር መሐመድ ባካሪ በሰጡት አስተያየት የሕብረተሰቡ እንቅስቃሴ የሚያነቃቃና ተስፋ የሚሰጥ ነው።

በጉብኝታቸው ያለቴክኖሎጂ ህዝቡን በማነሳሳት ብቻ የተጎዳ መሬት ድኖ ለልማት መዋሉን መመልከታቸውን ተናግረዋል ።

በዓለም ባንክ የስነ አካባቢ ዳይሬክተር ሚስስ ጁሊያ ባክናል በበኩላቸው፣ ፕሮከጅቱ በትግራይ ክልል ያለው አፈጻጸም ከሌሎች ሀገራት የተሻለ ስለመሆኑ በአካል ያዩበት እንደሆነ ተናገረዋል።

"በህዝብ ተሳትፎ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች መሬት ከመሸርሸርና መራቆት ድኖ የተረጋጋ የአየር ሁኔታ በማየቴ ተደስቻለሁ " ብለዋል ።

በአሜሪካ የስቴት ዲፓርትመንት ኢኮኖሚስት ሚስስ ርብቃ ፊሸር "ለዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮጀክት ያደረግነው ድጋፍ በተግባር ላይ እየዋለ መሆኑን አረጋግጠናል፤ በቀጣይ ሀብት በማሰባሰብ ድጋፋችንን እንቀጥላለን" ሲሉ ተናግረዋል።

የእንደርታ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋይ ገብረተኸለ እንዳሉት በአርሶአደሩ ተሳትፎ በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ከዚህ ቀደም በአካባቢው ተራቁተው የቆዩ አካባቢዎች በእፅዋት ተሸፍነዋል ።

ከ 2002 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ በሚገኙ 26 ወረዳዎች ሕብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ በትግራይ ግብርናና ገጠር ልማት የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ መሐሪ ገብረመድህን ናቸው።

በፕሮጀክቱ በተከናወኑ የተፋሰስ ልማትና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የተራቆቱ መሬቶችን በማዳን አካባቢውን ወደ አረንጓዴነት ለመቀየር መቻሉን ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ ከ70ሺህ በላይ አርሶአደሮች ተሳታፊ ሲሆኑ ለመሬታቸው የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸው መሬቸውን በዘላቂነት በመንከባከብና በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል

"አርሶ አደሩ ለይዞታው ዋስትና በማግኘቱ ከዚህ ቀደም ከእርሻ መሬት ወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና ግጭቶች ቀርተዋል " ብለዋል ።

በተለይም በፕሮጀክቱ የታቀፉ ወጣቶችና ሴቶች በለሙ ተፋሰሶች ውስጥ በንብ ማነብ፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ እንዲሁም በመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የስራ ባህላቸው አየጎለበተና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ መሆናቸውን አቶ መሀሪ አስታውቀዋል ።

የድድባ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተኪኤን ገብረ ጊዮርጊስ  በሰጡት አሰተያየት  ከሶስት ዓመት በፊት አካባቢያቸው አፈሩ የተሸረሸረ ፣ምንም አይነት ዛፍ የማይበቅልበትና የተራቆተ እንደነበር አስታውሰዋል ።

"በፕሮጀክቱ ታቅፈን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በመስራታችን  አካባቢው ወደ አረንጓዴነት ተለውጦ የደረቁ ምንጮች ውሀ ማፍለቅ ችለዋል " ያሉት አርሶአደሩ፣ ይህም የእንስሳት መኖ ከማግኘት ባለፈ በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶአደር ብርሃኑ ረዳ በበኩላቸው በፕሮጀክቱ ታቅፈን እርከን፣ የጎርፍ መቀልበሻና መከላከያ እንዲሁም የውሀ ማቆሪያ ጉድጓድ በመስራታችን መሬታችንን ማዳን ችለናል " ብለዋል ።

የማሳቸው ለምነተ በመመለሱና እርጥበት በመቋጠሩ በሄክታር ከ20 አስከ 25 ኩንታል ምርት እንዲያገኙ አግዟቸዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ