አርዕስተ ዜና

ደረጃቸውን ያልጠበቁ የአደባባይ ማስታወቂያዎች የመዲናዋን ገፅታ እያበላሹ ነው

08 Oct 2017
1281 times

አዲሰ አበባ መስከረም 28/2010 በመንገዶችና አደባባዮች ላይ የሚሰቀሉ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ማስታወቂያዎች የመዲናዋን ውበትና ገጽታ እያበላሹ መሆኑን የከተማዋ ውበት፣ መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ገለጸ።

አደባባዮችን በአግባቡ ማልማት የሚያስችል መመሪያ ማዘጋጀቱንና ከከተማ አስተዳደሩ እውቅና ውጪ በግለሰቦች ድርጅቶች የሚሰየሙ አደባባዮችን ወደ ስርዓቱ የማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልጿል።

የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ባልተገባ ሁኔታ የሚቀመጡ ማስታወቂያዎች በከተማዋ ውበት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው።

በመሆኑም አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ስርዓት ባልተከተለ መንገድ የተቀመጡ ማስታወቂያዎችን የማንሳት ሥራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ማስታወቂያዎቹ የከተማዋን ገጽታ ከማበላሸት ባለፈ ከዚሁ መገኘት የሚገባውን ገቢ እያሳጡ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ቀደም ሲል ወጥነት ያለው ደንብና መመሪያ ባለመቀመጡ በዚህ ተግባር በተሰማሩ ግለሰቦች ላይ የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩን የገለጹት ወይዘሮ አልማዝ የተዘጋጀው ደንብ አሰራሩን ስርዓት እንደሚያሲዘው አክለዋል።

ባለሃብቶች አደባባዮችን በማልማትና በማስዋብ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም ስያሜያቸውን እስከመቀየር መደረሱ ተገቢ ባለመሆኑ ወደ ስርዓቱ እንደሚገቡ ነው የገለጹት።

እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለጻ ኤጀንሲው የከተማዋ አደባባዮች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆነው እንዲለሙ ለማድረግ ከባለሃብቶች ጋር በቅርበት ይሰራል።

ኢጀንሲው አደባባዮችን ለማልማት ወስደው ሳያለሙ ለረጅም ጊዜ አጥረው ባስቀመጡ ባለሃብቶችና ግለሰቦች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድም ነው የተናገሩት።

በአዲስ አበባ 80 የሚሆኑ አደባባዮች መኖራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ