አርዕስተ ዜና

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት ለታዳጊ አገራት ማንቂያዎች ናቸው...የተለያዩ አገራት ሚኒስትሮች Featured

06 Oct 2017
1411 times

አዲስ አበባ መስከረም 26/2010 ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ የምታደርገው ጥረት ለታዳጊ አገሮች የማንቂያ ደወል እንደሆነ የተለያዩ አገራት ሚኒስትሮች ገለጹ።

የ47 ታዳጊ አገራት የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች በመጪው ህዳር ወር በጀርመን ቦን ከተማ ለሚካሄደው 23ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፍረንስ ለመዘጋጀት በአዲስ አበባ ምክክር አድርገዋል።

ተሳታፊዎቹ በኢትዮጵያ ከብክለት ነፃ የሆነው የከተማ ቀላል ባቡርና ግንባታው 97 በመቶ የተጠናቀቀውን የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጎብኝተዋል።

ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ከፀሀይ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፤ የተፈጥሮ ሀብቷን በመንከባከብ፤ የተፋሰስ ልማትን በማስፋፋትና የደን ልማት ስራ ላይ ትኩረት መስጠቷን ሚኒስትሮቹ በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል።

የዩጋንዳ ውሃና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ኪቱቱ ሜሪ ጎሬቲ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታከናውናቸው የዜሮ ብክለት ፕሮጀክቶች ለታዳጊ አገራት ማንቂያዎች ናቸው።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አፍሪካውያንና የአፍሪካ ህብረት ድምፃችንን ከፍ አድርገን ማሰማት አለብን ሲባል "እንደ ኢትዮጵያ ከበካይ ጋዝ ልቀት የጸዱ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ መሆን አለበት" ብለዋል።

"ዩጋንዳ በትራንስፖርት ዘርፍ ተመሳሳይ እቅድ አላት ፤ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያን ልምድ መውሰድ የተሻለ ነው፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ታዳጊ አገራትም ይህንን ተሞክሮ መውሰድ አለባቸው" ብለዋል ሚኒስትሯ ዶክተር ኪቱቱ ሜሪ ጎሬቲ።

የሌሶቶ ሃይልና የአየር ትንበያ ሚኒስትር ፍራንሲስ ህሎአሌ በጉብኝት ያየኋቸው ፕሮጀክሮች ከአየር ንብረት ጋር የተጣጣሙ በመሆናቸው ለሌሎች አገራትም ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የምትገነባቸው የኅብረተሰቡንና የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያሳድጉ እነዚህ ፕሮጀክቶች የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መሰረት ማድረጋቸው ልዩ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ ፍራንሲስ።    

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ