አርዕስተ ዜና

የታዳጊ አገራት የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በአዲስ አበባ በመምከር ላይ ናቸው Featured

05 Oct 2017
1643 times

አዲስ አበባ መስከረም 25/2010 ኢትዮጵያ "የአየር ንብረት ለውጥ አስቸኳይና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆን አለበት" የሚል አቋም እንዳላት የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ እ.ኤ.አ ከህዳር 2016 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ለ47 ታዳጊ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ሊቀመንበር እንድትሆን በሞሮኮ መዲና ማራካሽ ላይ መመረጧ ይታወሳል።

በዚህም የ47 ታዳጊ አገራት የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች በመጪው ህዳር  ጀርመን ለሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት 23ኛው የአየር ንብርት ለውጥ ኮንፍረንስ ቅድመ ዝግጅት ላይ በአዲስ አበባ መወያየት ጀምረዋል።

አፍሪካን ጨምሮ ታዳጊ አገሮች ለዓለም የአየር ንብረት መዛባት ያላቸው ድርሻ ከ 4 በመቶ እንደማይበልጥና በአንጻሩ ከበለጸጉት አገራት ቻይና 23 በመቶ፣ አሜሪካ 19 በመቶ እንዲሁም የአውሮፓ አገራት 13 በመቶ በመያዝ ለአየር ንብረት ለውጥ ቀዳሚ ናቸው።

አንድ ቢሊዬን የሚጠጋ ህዝብ ያላቸው ታዳጊ አገራት በየቀኑ የተለያዩ አደጋዎችን በማስተናገድ ዜጎቻቸው ህይወታቸውን በአስቸጋሪ መንገድ ይመራሉ ተብሏል።

በ 40 ዓመታት ውስጥ በታሪክ አስከፊ የተባለውና በባንግላዲሽና ኔፓል የደረሰው የጎርፍ አደጋ፣ ሚሊዬን ዜጎችን ለጉዳት፤ በሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለህልፈት መዳረጉ ይታወሳል።

በአፍሪካ በተመሳሳይ በሴራሊዮን በከባድ ዝናብ ምክንያት በተፈጠረ ጭቃ ከ አንድ ሺህ በላይ ሰዎች ሞት፤ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ በዚህ ጉባኤ ላይ እንዳሉት የበለጸጉ አገራት በሚፈጥሩት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ተጎጂዎች ታዳጊ አገራት ናቸው።

ታዳጊ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ቢሆንም በሚከሰተው አደጋ ቀዳሚ ተጠቂ በመሆናቸው አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላከል የታዳጊ አገራት መሪዎች አንድነት በመፍጠር ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት አለባቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር አንድሬስ ጋርደር አገራቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተፈረመውን የፓሪሱን ስምምነት ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

ኖርዌይ እ.ኤ.አ በ 2050 የበካይ ጋዝ ልቀቷን ከ 80 አስከ 95 በመቶ ለመቀነስ ባስቀመጠችው እቅድ መሰረት እየተንቀሳቀሰች መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ ታዳጊ አገሮች ለሚያደርጉት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በሁለትዮሽም ሆነ በጋራ ግንኙነቶች የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ