አርዕስተ ዜና

ከቆቃ ወንዝ የሚለቀቀው ውሃ ጉዳት እንዳያስከትል ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ ነው

13 Sep 2017
2189 times

አዲስ አበባ መስከረም 3/2010 ከቆቃ ወንዝ የሚለቀቀው ውሃ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ለመቆጣጠር በሚያስችል መልኩ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ግዛው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በነሐሴ መጨረሻ በተለይም ጳጉሜን ሶስት በከፍታ ቦታዎች፣ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ የጣለው ዝናብ ግድቡ ከ20 ሴንቲ ሜትር በላይ እንዲጨምር አድርጓል።

በዚህም ግድቡ ሞልቶ የጎርፍ አደጋ ማስከተሉን ጠቁመው፤ ግድቡ ውስጥ ያለውን ከመጠን ያለፈ ውሃ ለመቀነስ ውሃ የመልቀቅ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ከግድቡ የሚለቀቀው ውሃ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል መቆጣጠር የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጎርፍ መከላከያ ፉካዎችን ከፍታ መጨመር፣ ከፍታ መጨመር በማይቻልባቸው ቦታዎችና አካባቢዎች በማዳበሪያ አፈር ሞልቶ በመደርደር ከፍታ የመጨመር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ጎርፉ ሲጥላቸው የፍሰት አቅጣጫ ማስቀየር የሚችሉ ዛፎችን ቆርጦ የማንሳት፣ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ በቂ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር የማድረግ ሥራም እየተከናወነ መሆኑን አቶ ጌታቸው አክለዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የመስተዳደር አካላት፣ በአካባቢው በሸንኮራ አገዳ ልማትና በአፋር ክልል በጥጥ ለቀማ ተሰማርተው የሚገኙ የጉልበት ሠራተኞች የጎርፍ አደጋውን ለመከላከል እየተረባረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን ጎርፉ በሰውና በንብረት ላይ አደጋ እንዳላስከተለ ጠቁመው፤ አደጋው እየባሰ ከመጣ በመከላከል ሥራው የአገር መከላከያ ሰራዊት በቀጣይ እንደሚሳተፍ አስታውቀዋል።

ደቡብ ምዕራብ ዞን ኢሉ ወረዳ ልዩ ዞን፣ ሰበታ ሀዋዝ ወረዳ፣ ሊበን፣ በዱለቻና ቆቃ ግድብ ከመድረሱ በፊት ያሉት አካባቢዎች ላይ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ነዋሪዎቹ እንደተፈናቀሉ ገልጸዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ