አርዕስተ ዜና

በትግራይ የአረንጓዴ ልማት ሥራው ለክልሉ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው Featured

12 Sep 2017
2225 times

መቀሌ መስከረም 2/2010 የአረንጓዴ ልማት ሥራው በክልሉ እየተመዘገበ ላለው የኢኮኖሚ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቦ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የተከናወኑት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች በክልሉ ለተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት የጎላ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ።

በተለይም ለግብርና ልማት አመቺ ስነምህዳር ለመፍጠር ማስቻላቸውን አስረድተዋል።

በተጨማሪም የመስኖ ልማት ሥራው እንዲያድግና የተጠቃሚ አርሶአደሮች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋፆ ማድረጉን ጠቅሰዋል ።

በዚህም በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት የክልሉ የመስኖ ልማት ሽፋን 258 ሺህ ሄክታር መድረሱንና ይህም ከቀዳሚው አመት በ20 ሺህ ሄክታር ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የመስኖ ልማት ሥራው እየጎለበተ መምጣት የአርሶአደሩንና የክልሉን የግብርና ምርታማነት ከጊዜ ወደጊዜ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያጎለበተው መሆኑንም አመልክተዋል። 

በአረንጓዴ ልማት ሥራዎች በግብረናው ዘርፍ ለተመዘገበው ውጤት በዋናነት መጠኑ እየጨመረ የመጣው የከርሰና የገፀ ምድር ውሃ የጎላ አስተዋጽኦ ማድረጉን ዶክተር አትንኩት ገልጸዋል፡፡

"በአረንጓዴ ልማት ሥራው በተመዘገበው ውጤት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራውን ጨርሰናል ማለት አይደለም" ያሉት ዶክተር አትንኩት፣ በቀጣይ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ሥራዎችን ለማከናወን ዕቅድ መያዙን ገልፀዋል።

"ለዚህም ከከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በክልሉ ሕዝብ ነጻ የጉልበት አስተዋጽኦ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች መሰራታቸውን ያስታወሱት ደግሞ በቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ክብካቤ ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ሀፍቱ ኪሮስ ናቸው።

በተከናወኑ ሥራዎች የአፈር መሸርሸርና የደን መመናመንን ለመቀነስ መቻሉን ጠቅሰው ህዝቡ ከልማት ሥራው ቀጥተኛ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ለሁሉም የግብርና ሥራዎች መሰረት እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ በክልተ አውለአሎ ወረዳ የአብረሀ ወአፅበሀ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሊቀመንበር አርሶአደር ገብረሚካኤል ግደይ ናቸው፡፡

በቀበሌው እርሳቸውን ጨምሮ 900 አባወራ አርሶአደሮች በመስኖ ልማት ሥራ መሳተፋቸውን ገልጸው፣ በየዓመቱ እስከ አምስት ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ጥሩ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አርሶአደሩ እንዳሉት በቀበሌው በሚገኙ የጎርፍ መውረጃ ጅረቶች ላይ በእያንዳንዳቸው እስከ 13 የሚደርሱ  የውሃ መያዣ አነስተኛ ግድቦች ተገንብተው አርሶአደሩ አማራጭ ውሃ እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡

በሳዑዲ አረቢያ ከስደት ተመልሶ ወደ እንስሳት ሀብት ልማት ሥራ መግባቱን የተናገረው  በአፅቢ ወንበርታ ወረዳ ሀየሎም ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ርዕሶም ኃይሉ

እንዳለው አሁን ላይ የ50 ዘመናዊ የንብ ቆፎች ባለቤት እንዲሆን ያደረገው በአካባቢው ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በመከናወኑ ነው፡፡

ባለፉት ሁለት የክረምት ወራት ካመረተው 150 ኪሎ ግራም ማር ሽያጭ ከ22ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘቱንና እስከሚቀጥለው ህዳር ወር 2010ዓ.ም ድረስ ደግሞ ተጨማሪ ምርት እንደሚጠብቅ አስታውቋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ