አርዕስተ ዜና

አፍሪካዊያን ህገ ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውርን ለመከላከል መቀናጀት አለባቸው

08 Sep 2017
2333 times

አዲስ አበባ ጳጉሜ 3/2009 አፍሪካዊያን ህገ ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውርን ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የዓለም አቀፉ የአደንዛዥ ዕጽና የሕግ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ረዳት ጸሃፊ ዳን ፎቴ ተናገሩ።

ቢሮው በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በአፍሪካ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውር ለመከላከል የስልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

አፍሪካዊያን ህገ ወጥ ዝውውሩን ለማስቆም ምን ማድረግ እንዳለባቸውና ቢሮው በሚያደርገው ድጋፍ ዙሪያ ከአህጉሪቱ ጋዜጠኞች ጋር የስልክ ኮንፈረንስ አካሂደዋል።

በአፍሪካ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውር ለመከላከል አገራት ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ በማውጣት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

የዝሆን፣ ነብር፣ አውራሪስና ሌሎች የዱር እንስሳት ዝውውር በስፋት የሚከናወንባቸው እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳን ያሉ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የጋራ የህግ ማዕቀፍ ሊኖራቸው ይገባል ነው ያሉት።

ህገ ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውር የዓለም የጸጥታ ስጋትም እንደሆነ የጠቆሙት ሚስተር ዳን ፎቴ አደጋውን ለመከላከል የአሜሪካ መንግስት ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት፣ አጋር አካላትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸውና በቀጣይም ቅንጅታቸውን በማጠናከር የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አክለዋል።

አገራት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን በማጠናከር ህገ ወጥ ዝውውሩን እንዲከላከሉና ለብሄራዊ የዱር እንስሳት መጠለያዎች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርጉ ድጋፋችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

በአፍሪካ በዱር እንስሳት ጥበቃና ደህንነት ላይ ለሚሰሩ ዓለም አቀፍ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስልጠና እንደሚሰጡም ተናግረዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ