አርዕስተ ዜና

በሚቀጥለው ወር የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች እርጥበቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሜቲዎሮሎጂ Featured

07 Sep 2017
2491 times

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2009 በሚቀጥለው ወር በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች የእርጥበቱ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ገለጸ።

 ከነሀሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ከባድ ዝናብ በሚጠበቅባቸው አካባቢዎች እርጥበቱ ከመጠን በላይ ሊሆን ስለሚችል ቦይ በማውጣት ፣ የማጠንፈፍና የመከላከል ሥራ በመሥራት ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ኤጀንሲው አሳስቧል፡፡

 እንዲሁም  አረምን በወቅቱ በማረም ከግብርና ባለሙያ በሚያገኙት ምክረ ሀሳብ በመደገፍ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ነው የገለፀው፡፡

 ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው አብዛኛው ኦሮሚያ ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ፣ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እርጥበት እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡

 ይህም በተለይ ዘግይተው ለተዘሩ፣ በእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙትም ሆነ ፍሬ በመሙላት ላይ ላሉት ሰብሎች እንዲሁም ለቋሚ ተክሎች የውኃ እርጥበቱ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

 በተጨማሪም ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለእፅዋት ልምላሜና ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት መሻሻልና ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት ለደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ገልጿል፡፡

 የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ በረባዳማ፣ ውኃ ገብና በወንዝ ዳርቻ ባሉ ማሣዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል በተጠቀሱት አካባቢዎች ተገቢው የመከላከል እርምጃ ቢወሰድ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ይቻላል ብሏል፡፡

 በሌላ በኩል በአብዛኛው ቦታዎች የተሻለ ዝናብ ቢጠበቅም አልፎ አልፎ እጥረት እንደሚኖር ታሳቢ በመደረጉ ውኃን ጠብቆ የማቆየቱና የማሰባሰቡ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ኤጀንሲው በላከው መግለጫ አስገንዝቧል፡፡

 አብዛኛው የአባይ፣ የተከዜ፣ የባሮአኮቦ፣ የኦሞጊቤ እንዲሁም ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛውና መካከለኛው አዋሽ፣ የላይኛው ዋቢሸበሌና ገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡

 በተጨማሪም በተለይ በአገሪቱ ምዕራባዊ አጋማሽና በመካከለኛ ከፍተኛ ቦታዎች በሚገኙ አንዳንድ ተፋሰሶች ላይ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችልም ትንበያው ይጠቁማል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ