አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የኬሚካል ተረፈ ምርቶች በሰውና በአካባቢ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ በቂ ጥንቃቄ እየተደረገ አይደለም

11 Aug 2017
1397 times

አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2009 ከኬሚካል አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ ተረፈ ምርቶች/በካይ ኬሚካሎች/ በሰውና በአካባቢ  የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ የሚከናወነው ሥራ በቂ አይደለም ሲሉ ባለሙያዎች ገለጹ።

ባለሙያዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳስታወቁት ከተለያዩ የኬሚካል ውጤት አምራች ፋብሪካዎች ወደ አካባቢ የሚለቀቀው ተረፈ ምርት በቂ ጥንቃቄ ተደርጎበት አይደለም።

አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች በተረፈ ምርት አወጋገድ ላይ በወጣው መመሪያ መሰረት እየሰሩ አለመሆኑንም ተናግረዋል።

የጽዳት መገልገያዎች፣የፕላስቲክ ውጤቶች፣የውሃ ማከሚያ፣የወረቀት ማቅለሚያና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማምረቻ ፋብሪካዎች ከኬሚካል ኢንዱስትሪዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬሚካል ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ብርሃኑ አሰፋ የኬሚካል ኢንዱስትሪው አጠቃላይ ለአገሪቷ ኢንዱስትሪ ልማትና ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይገልጻሉ።

ይሁን እንጂ አገሪቷ ካለችበት የዕድገት ደረጃ አኳያ የተረፈ ምርት አወጋገድ ስርዓቱም በዚያው መጠን እንዲያድግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት አይደለም ብለዋል።

ከኬሚካል ኢንዱስትሪው የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን አወጋገድ ችግር የሚያቃልሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባም ነው ምሁሩ የገለፁት።

የኬሚካል ተረፈ ምርቶች በአግባቡ ካልተወገዱ በተለይም በወንዞች ላይ የሚያደርሱት ብክለት አደገኛ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ብርሃኑ የተበከሉ ወንዞችን ለማከም የሚወጣው ወጪም በአገር ሀብት ላይ የሚያስከትለው ኪሳራ  ቀላል አለመሆኑን አስረድተዋል።

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች አንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃዱሾም ጥሁም እንደሚሉት አብዛኞቹ የኬሚካል አምራች ኢንዱስትሪዎች የተረፈ ምርት አወጋገድ መመሪያውን መሰረት አድርገው እየሰሩ አይደለም።

ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ በማያስወግዱና አካባቢ ላይ ጉዳት በሚያደርሱ ኢንዱስትሪዎች ላይም የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

የተረፈ ምርት አወጋገድ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ፣ኦሮሚያ፣ትግራይና ደቡብ ክልሎች የፕላስቲክ አወጋገድ ላይ ጥናት መደረጉንም አቶ ሃዱሾም ገልጸዋል።

ጥናቱ የአገሪቷ የኬሚካል ውጤቶች ተረፈ ምርት አወጋገድ ስርዓቱ ዝቅተኛ መሆኑንና  ብዙ መሰራት እንዳለበት ማመላከቱን ነው የተናገሩት።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አለሙ ስሜ በበኩላቸው በ2010 በጀት ዓመት ከማንኛውም ኢንዱስትሪ የሚወጡ ተረፈ ምርቶች በሰውና አካባቢ ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራበታል ብለዋል።

የተረፈ ምርት አወጋገድ ችግርን በተደራጀ ሁኔታ ለመፍታት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ቀደም ሲል እንዲህ አይነት ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስርዓት እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ