አርዕስተ ዜና

በጉጂ ዞን ከ19 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው

10 Aug 2017
1862 times

ነገሌ ነሃሴ 4/2009 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በበጋ ወራት በአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በተከናወነበት 19 ሺህ 772 ሄክታር መሬት ላይ የችግኝ ተከላ እየተከናወነ ነው፡፡

የችግኝ ተከላ ስራ በመካሄድ ላይ ያለው ካለፈው መጋቢት ወር 2009 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ መሆኑን የዞኑ ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ አለሙ በጄ ገልፀዋል፡፡

እስካሁን በተካሄደው ጥረት ለተከላ ከተዘጋጀው 142 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ 126 ሚሊዮኑ ተተክሏል፡፡

ቀሪው ችግኝ እስከተያዘው ወር መጨረሻ ድረስ እንደሚተከል ተናግረዋል፡፡

በዚህ አመት ለተከላ የተዘጋጀው ችግኝ ካለፈው አመት በሶስት ሚሊዮን የተዘጋጀ መሬት ደግሞ በሰባት ሺህ ሄክታር ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

ችግኝ ከማዘጋጀት እስከ ተከላ በመሳተፍ ላይ ካሉት 64 ሺህ 813 አርሶ አደሮች መካከል 10 ሺህ 100 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡

በዞኑ እየተተከሉ ያለው የደን ፣ የእንስሳት መኖ ፣ የጥላ ዛፍና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሚታ ያለው የፍራፍሬ ችግኝ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጉጂ ዞን ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ግንቦት 15 የበልግ ፣ ከሀምሌ መጨረሻ እስከ ጥቅምት 15 ደግሞ የመኸር ዝናብ ተጠቃሚ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

የዞኑ 199 ሺህ ሄክታር መሬት የተለያዩ ዝርያ ባለቸው ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ደን የተሸፈነ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የአዶላ ወረዳ መሲና ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አደር አስረዲን ሀሮ እንደገለፁት ችግኝ መትከልና መንከባከብ ''የኦሮሞ ህዝብ ባህል በመሆኑ በየአመቱ የተለያዩ ችግኞችን በመትከል የውዴታ ግዴታየን እየተወጣሁ ነው'' ብለዋል፡፡

በተያዘው ክረምትም ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመተባበር በሳምንት ሁለት ቀን በበጋ ወቅት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ባከናወኑበት መሬት ላይ የጽድ ፣ የግራቪሊየና የዋንዛ ችግኝ መትከላቸውን ገልጸዋል፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ