አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ኢትዮጵያ በኤርትራ ድንበር የሚገኙ የሜዳ አህዮች ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ልታስመዘግብ ነው

09 Aug 2017
2312 times

አዲስ አበባ ነሃሴ3/2009 ኢትዮጵያ በኤርትራ ድንበር የሚገኙ የሜዳ አህዮች ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለዓለም አቀፉ ተሰዳጅ የዱር እንስሳት ኮንቬንሽን ልታስመዘግብ መሆኑን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የኮንቬንሽኑ አባል የሆኑ የአፍሪካ አገራት በህዳር 2010 ዓ.ም በፊሊፒንስ ለሚካሄደው 12ኛው ዓለም አቀፍ የተሰዳጅ የዱር እንስሳት ኮንቬንሽን ዝግጅት በአዲስ አበባ ውይይት እያካሄዱ ነው።

በውይይቱ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣንን የወከሉት አቶ ካህሳይ ገብረ ትንሳኤ ኢትዮጵያ የኮንቬንሽኑ አባል በመሆኗ፤ በድንበሯ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የዱር እንስሳት ተመዝግበው ልዩ ጥበቃ እንዲያገኙ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው11ኛው ኮንቬንሽን ኢትዮጵያ  በደቡብ ሱዳን ድንበር የሚገኙ የነጭ ጆሮ ቆርኬ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው።

በቀጣይ ዓመት በፊሊፒንስ ለሚካሄደው 12ኛው ዓለም አቀፍ የተሰዳጅ የዱር እንስሳት ኮንቬንሽን በኤርትራ ድንበር የሚገኙ የሜዳ አህዮች ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የምታስመዘግብ መሆኗንም ተናግረዋል።

የዱር እንስሳቱ በኮንሼንሽኑ መመዝገባቸው፣ አገራቱ ለእንስሳቱ ልዩ ጥበቃ እንዲያደርጉላቸው መሆኑን አቶ ካህሳይ ተናግረዋል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ መዓዛ ገብረመድኅን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በ2002 ዓ.ም የኮንቬንሽኑ አባል ከሆነች ጀምሮ ድንበር አቋርጠው ለሚመጡ እንስሳት ጥበቃ እያደረገች መሆኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና በዱር እንስሳት ስደት በዓለም ሁለተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንስሳቱን ከሕገ-ወጥ አደን ለመከላከል የኮንቬንሽኑን መሠረታዊ መርሆች በማክበር ከአጋር አካላት ጋር ጥበቃ እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ሱዳንና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ ባለ ነጭ ጆሮ ቆርኬ በመጠለያነት እያገለገለ መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። 

ዛሬ በተጀመረው  ጉባዔ  ከ42 የአፍሪካ አገሮች የመጡ ባለሙያዎችና ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

12ኛው የዓለም አቀፍ ተሰዳጅ የዱር እንስሳት ኮንቬንሽን በመጪው ሕዳር መጀመሪያ በፊሊፒንስ ይካሄዳል።

ዓለም አቀፉ ተሰዳጅ የዱር እንስሳት ኮንቬንሽን በአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ድንበር አቋርጠው የሚሰደዱ እንስሳት ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚሰራ ተቋም ነው።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ