አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገፅታዎች በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የአገሪቱ አካባቢዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ Featured

03 Aug 2017
2426 times

አዲስ አበባ ሀምሌ 27/2009 ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገፅታዎች በሚቀጥሉት አስር ቀናት በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ተነበየ።     

ሊጠናከሩ ከሚችሉ የደመና ክምችቶች ቅፅበታዊ ጎርፍና አልፎ አልፎም በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ሊከሰት እንደሚችልም ኤጀንሲው ገልጿል።   

በዚህ መሰረት ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ምዕራብና ሰሜን ሸዋ፣ የአርሲና የባሌ ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ የጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፣ ከአማራ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ የባህዳር ዙሪያ፣ አዊ ዞን፣ የሰሜንና የደቡብ ጎንደር ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።   

በተመሳሳይ የትግራይ ዞኖች፣ ከደቡብ ክልል ደግሞ ሀዲያና ጉራጌ ዞኖች፣ የከፋና ቤንች ማጂ፣ የወላይታ፣ ሲዳማና ጌዲዮ ዞኖች በአብዛኛው መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚያገኙ ይሆናል።   

ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ከአፋር ክልል ደግሞ ዞን 3 እና ዞን 5፣ ከሶማሌ ክልል የጅግጅጋና ሲቲ ዞኖች፣ ድሬዳዋና ሐረሪ በአብዛኛው ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙም ኤጀንሲው ጠቁሟል። 

በሌላ በኩል የደቡብ ኦሞና አጎራባች የሰገን ህዝቦች ዞኖች በአብዛኛው ደረቃማ የአየር ሁኔታ እያመዘነባቸው አነስተኛ ዝናብ ያገኛሉ ብሏል። 

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምቱ ዝናብ በመጠንና በስርጭት ዝናብ በሚያገኙ ተፋሰሶች ላይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ኤጀንሲ ያስታወቀው።  

በዚህም በአብዛኛው ተከዜ፣ አባይ፣ ባሮአኮቦ፣ ኦሞጊቤ፣ የላይኛውና መካከለኛው አዋሽና ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛው ገናሌዳዋና ዋቢ ሸበሌ፣ ጥቂት የላይኛው አፋር ደናከል ተፋሰሶችም መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል።

የታችኛው አዋሽ፣ ስምጥ ሸለቆና ባሮአኮቦና የመካከለኛው ዋቢ ሸበሌ ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል ሲል ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። 

የዝናብ ስርጭታቸው ከመደበኛ በላይና ከባድ ዝናብ በሚጠበቅባቸው አካባቢዎች የወንዞች ሙላት እንዲሁም የጎርፍና የመሬት መንሸራተት ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ኤጀንሲው አሳስቧል። 

ወሩ በአብዛኛው የመኸር አብቃይ አካባቢዎች ከእርጥበታማ እስከ በጣም እርጥበታማ የአየር ሁኔታ እንደሚያመዝን ያብራራው ኤጀንሲው ይህም ለተያዘው የግብርና ሥራ ገንቢ ሚና እንደሚኖረው ነው የገለጸው።  

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ